በክልሉ ሠላማዊ የመማር ማስተማሩን ስራን ለማስቀጠል ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራት ይጠበቅባቸዋል - አቶ ኦርዲን በድሪ

78

ሐረር ፣የካቲት 9/2013(ኢዜአ) በሐረሪ ክልል የመማር ማስተማር ሂደቱ ምቹና ሠላማዊ እንዲሆን ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራት እንደሚጠበቅባቸው የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ገለጹ፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ  ከወረዳ አመራሮችና የፀጥታ አካላት ጋር በወቅታዊ  ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡

በውይይቱ ወቅት  እንደተናገሩት፤ በክልሉ አንዳንድ ትምህርት ቤቶች ላይ የመማር ማስተማሩን ሂደት ለማደናቀፍ የጥፋት ተላላኪዎች ተማሪዎችን ሽፋን በማድረግ ሁከት ለመፍጠር ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡

ድብቅ የፖለቲካ አጀንዳዎችን በማራመድ የመማር ማስተማር ሂደት ለማደናቀፍ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን ሁሉም ማህበረሰብ ማጋለጥ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

በተለይም የወረዳ አመራሮችና የፀጥታ አካላት የመማር ማስተማሩ ስራ ሠላማዊ ሆኖ እንዲቀጥል በቅንጅት መስራት እንደሚጠበቅባቸው  ገልጸዋል፡፡

ትምህርት ቤቶች ተማሪዎቻቸውን  በእውቀትና ክህሎት የሚበቁበት እና ከማንኛውም የፖለቲካ እንቅስቃሴ ነፃ ናቸው ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ፤ በዚህ ጉዳይ ላይ የመምህራን ፣የተማሪ ወላጆች እና ሌሎች አካላትን ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ መካሄድ እንዳለባቸው  ተናግረዋል፡፡

የወረዳ አመራሮች የአካባቢያቸውን ሠላም ለማስጠበቅ ከፀጥታ አካላት ጋር በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው ያሳሰቡት ደግሞ የክልሉ ሠላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ሃላፊ አቶ ናስር ዩያ ናቸው፡፡

በተለይም በየትምህርት ቤት አካባቢ የሚደረጉት ፀረ ሠላም እንቅስቃሴዎችን በመከታተል አጥፊዎችን  ለህግ ማቅረብ ይገባል ብለዋል፡፡

ወጣቱ በሀሰተኛ የማህበራዊ ትስስር ገፆች  አፍራሽና በሬ ወለድ ሃሳቦች ተጋላጭ እንዳይሆን  የማስገንዘብ ስራው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አስገንዝበዋል፡፡

በክልሉ ምክር ቤት መሰብሰቢያ አዳራሽ በተካሄደው የውይይት መድረክ የወረዳ አመራሮች፣ የፀጥታ አካላት እና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም