በአማራ ክልል የአገልጋይነት እሴት የተላበሰ የመንግስት ሠራተኛ አቅም ለመገንባት እየተሰራ ነው

73

ባህር ዳር ፤ጥር 09/2013 (ኢዜአ)፡ - በአማራ ክልል የአገልጋይነት እሴትና መልካም ሥነ -ምግባርን የተላበሰ የመንግስት ሠራተኛ አቅም ለመገንባት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ገለጸ።

በተሻሻሉ የአገልግሎት መመሪያዎች ዙሪያ  ግንዛቤ ለማስጨበጥ ከምዕራብ አማራ ለተወጣጡ የሲቪል ሰርቪስ መስሪያ ቤቶች ኃላፊዎችና ባለሙያዎች የተዘጋጀ ስልጠና ዛሬ በባህር ዳር ከተማ  ተጀምሯል።

የክልሉ ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽነር ሙሉቀን አየሁ ስልጠናው ሲጀመር እንዳሉት በመንግስት ተቋማት የሚታዩ የአገልግሎት አሰጣጥና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት በትኩረት እየተሰራ ነው።

በቂ ዕውቀትና ክህሎት ባለው አነስተኛ የሰው ኃይል ውጤታማ ስራ በማከናወን የመንግስት ሠራተኛው  ተወዳዳሪና ተመራጭ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

ለዚህም ኮሚሽኑ  ለመልካም አስተዳደርና አገልግሎት አሰጣጥ እንቅፋት የሆኑ መመሪያዎችን ለይቶ በማሻሻል ለአሰራር ምቹ የማድረግ ስራ እያከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።

እንደ ሃገር በቅርቡ  በሲቪል ሰርቪሱ ላይ  ይፋ የተደረገው ጥናት እንደሚያመለክተው  አንድ ሰራተኛ በቀን ስምንት ሠዓት መስራት ሲገባው  የሚሰራው ከሁለት  እስከ አራት ሠዓት ብቻ እንደሆነ ተረጋግጧል ብለዋል።

ለችግሩ ዋነኛው መንስኤ ደግሞ ዘርፉን እየገመገመ የሚመራ ተቋም ካለፉት ሶስት ዓመታት ወዲህ ባለመኖሩ እንደሆነ ጠቅሰው፤ ችግሩን ለመፍታት በቀጣይ የሚከታተልና የሚቆጣጠር ተቋም እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

ስልጠናውም በተሻሻሉ የምልመላና መረጣ፣ የተፈላጊ ችሎታ፣ የመንግስት ተሿሚዎች ከኃላፊነት ሲነሱ አመዳደብ፣ ትምህርታቸውን ያሻሻሉ አመራሮችና ሙያተኞች አመዳደብ፣ ፈቃድ አሰጣጥና የህክምና ማስረጃ አቀራረብ በሚሉና ሌሎች መመሪያዎች ላይ እንደሚያተኩር ኮሚሽነሩ አመላክተዋል።

የተዘጋጁት መመሪያዎችም በየጊዜው በበራሪ ወረቀት የምንልካቸውን አሰራሮች በማስቀረት ከላይ እስከ ታች ወጥ የሆነ አሰራርን ተግባራዊ በማድረግ ችግሩን የሚያቃልሉ ናቸው ብለዋል።

ሰልጣኞችም የሚሰጠውን ትምህርት  በአግባቡ በመከታተል የአገልጋይነት እሴትና መልካም ሥነ-ምግባርን ተላብሰው ለተገልጋዩ ህብረተሰብ የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዲሰጡ አሳስበዋል።

ለአምስት  ቀናት በሚቆየው ስልጠና  በምዕራብ አማራ ከሚገኙ ዞኖች፣ ወረዳዎችና ከክልል ቢሮዎች የተውጣጡ ከ300 በላይ የሲቪል ሰርቪስ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም