በአሮሚያ 3 ዞኖች ለመንግስት ሠራተኞች የአቅም ግንባታ ሥልጠና እየተሰጠ ነው

106

አምቦ፤ ነገሌ፤ ጅማ፤ የካቲት 08/2013(ኢዜአ)፡- በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ፣ ጉጂ እና ጅማ ዞኖች ''የመንግስት ሠራተኞች የአገልጋነት ስሜት ተላብሰን ህዝባችንን እናገልግል'' በሚል መሪ ሀሳብ ለመንግስት ሠራተኞች የአቅም ግንባታ ሥልጠና እየተሰጠ መሆኑን ተገለጸ።

የምዕራብ ሸዋ ዞን የሰው ሃይል አቅም ግንባታና አስተዳደር ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ባንዲራ ገላና በአምቦ ከተማ ዛሬ በተጀመረው የሥልጠና መድረክ እንደገለጹት በዞን ደረጀና 22 ወረዳዎች የሚገኙ 11ሺህ145 የመንግስት ሠራተኞች በሥልጠናው እየተሳተፉ ነው።፡

ለአራት ቀናት የሚቆይ የሥልጠናው ዓላማ አሁን ባለው ወቅታዊ ሁኔታ የመንግስት ሠራተኞች በሀገሪቱ የመጣውን ለውጥ በጥልቀት በመረዳት ለስኬታማነቱ የድርሻቸውን እንዲወጡ ለማስቻል መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በዚህም የመጣውን ሪፎርም እንዴት ማስቀጠል ፣ በማህበራዊና ኢኮኖሚዊ እንቅስቃሴ ውስጥ የመንግስት ሠራተኞች ሚና በሚሉ ርዕሶች ዙሪያ ትምህርት እንደሚሰጥ አመልከተዋል፡፡

በተመሳሳይ በጉጂ ዞን ከ12 ሺህ በላይ የመንግስት ሠራተኞች የተሳተፉበት ሥልጠና ተጀምራል።

በነገሌ ከተማ የጀመረውን ሥልጠና የከፈቱት የዞኑ ምከትል አስተዳዳሪ አቶ ተሾመ ከበደ እንዳሉት ሠራተኛው የተገልጋዩን ህዝብ ፍላጎት ለማርካት በተመደበበት የሥራ ዘርፍ ቀልጠፋ አገልግሎት መስጠት ይጠበቅበታል።

በሀገራዊ ለውጡ የተገኙ ውጤቶች ማጠናከር እና ተግዳሮቶች መሻገር በሚቻልበት ዙሪያ በዞኑ ሁሉም ወረዳዎች ለሚገኙ የመንግስት ሠራተኞች ሥልጠናው መስጠት መጀመሩንም አስታውቀዋል፡፡

ከለውጡ በፊት የነበሩ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ደረጃ በደረጃ እየተፈቱ ቢሆንም ሙሉ በሙሉ ለመፍታት ሠራተኛው ሥልጠናውን በተገቢው በመከታተል በተመደበበት የስራ ዘርፍ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እራሱን ከወዲሁ እንዲዘጋጅ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በጅማ ዞን በየደረጃው ለሚገኙ የመንግስት ሠራተኞች ሥልጠና እየተሰጠ ይገኛል።

ሥልጠናው ፈጣን እና በቂ አገልግሎት ለተገልጋይ በመስጠት ስር ነቀል ለውጥ ለማምጣት የተዘጋጀ መሆኑን የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ አብዱላኪም ሙሉ ገልጸዋል፡፡

ጠንካራ የማህበረሰብ አገልጋይ እንዲኖርና የተገልጋይ እርካታን ማምጣት የሚቻልበትን ሁኔታዎች ማመላከት አስፈላጊ በመሆኑ ሥልጠናው በየደረጃው ለሚገኙ የመንግስት ሠራተኞች ከዛሬ ጀምሮ ለአራት ቀናት እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡

በአገልግሎቱ ዘርፍ ለውጥ በማምጣት ሀግራዊ ለውጡ ለሁሉም ተደራሽ መሆን እንዲችል የመንግስት ሠራተኛው ሚናው ከፍ ያለ ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም