በውርስ ያገኘሁትን በህግ አግባብ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ማግኘት አልቻልኩም-ቅሬታ አቅራቢ

172
አዲስ አበባ ሃምሌ 19/11/2010 በአዲስ አበባ ከተማ የካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ወርቅዬ ደበላ የአምስት ልጆቻቸውን አባት የሃምሳ አለቃ መንግስቱ አለሙ በሞት ከተለዩዋቸው 25 ዓመት ሆኗቸዋል። ባለቤታቸው በኑዛዜ ያወረሷቸው 253 ካሬ ሜትር ቦታና መኖሪያ ቤት ከልጆቻቸው ጋር ወራሽ መሆናቸውን በፍርድ ቤት አረጋግጠዋል። በአሁኑ ወቅት በወራሽነት ላገኙት ቦታና መኖሪያ ቤት በስማቸው ግብር እየከፈሉ መሆናቸውን በእጃቸው የሚገኙ ሰነዶች የሚያስረዱ ቢሆንም የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ሊያገኙ አለመቻላቸውን ይናገራሉ። ፍርድ ቤት ባረጋገጠላቸው ይዞታ ላይ ወረዳ 7 መኖሪያ ቤት የሰራበት መሆኑን የገለጹት ወይዘሮ ወርቅዬ ይህን ቅሬታቸውን ለወረዳው አስተዳደር ቢያቀርቡም የእርሳቸው አለመሆኑን በመግለጽ ምላሽ እንደተሰጣቸው ተናግረዋል። ቅሬታ አቅራቢዋ ፍርድ ቤት ያረጋገጠላቸው ይዞታ ተቀንሶ የተሰጣቸው የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ 104 ካሬ ሜትር ብቻ እንደሆነ የተናገሩት ወይዘሮዋ ትክክለኛው ይዞታዬ ይረጋገጥልኝ ሲሉ ቅሬታቸውን አቅርበዋል። ባለመማራቸውና ሴት በመሆናቸው አስተዳደሩ በደል እየፈጸመባቸው እንደሆነ የሚያምኑት ወይዘሮ ወርቅዬ ወረዳውም ሆነ ክፍለ ከተማው በአግባቡ እንደማያስተናግዳቸው ገልጸዋል። ወይዘሮ ወርቅዬ እና ልጆቻቸው የሚኖሩበት መኖሪያ ቤት በእርጅና ምክንያት እየፈረሰ ያለ ሲሆን የክረምት ወቅት በጣም እየተቸገሩ መሆኑን ገልጸው ቤቱን ለማደስና የውኃ መውረጃ ለማሰራትና እድሳት ለማድረግ ወረዳው እንደከለከላቸው ተናግረዋል። ልጃቸው ወጣት ቃልኪዳን መንግስቱ እንደሚለው ከወላጅ አባታቸው በውርስ ያገኙት ቦታ ማስረጃ ቢኖረውም የየካ ክፍለ ከተማ መሬት አስተዳደር ሙሉ የመሬቱን ይዞታ የሚገልጽ ማስረጃ ሊሰጣቸው እንዳልቻለ ተናግሯል። የየካ ክፍለ ከተማ ይዞታ አስተዳደር ኃላፊ አቶ ክብሮም አሰፋ በቀረበው ቅሬታ ላይ በሰጡት ምላሽ ከይዞታው መስራች የሃምሳ አለቃ መንግስቱ አለሙ ወደ እነ ወርቅዬ ደበላ ሲዞር በ1999 ዓ.ም የተሰጣቸው የተነጻጻሪ ካርታ 104 ካሬ ሜትር እንደሆነ ተናግረዋል። ቅሬታ አቅራቢዋ ትክክለኛ ይዞታዬ 253 ካሬ ሜትር ነው ብለው ቢከራከሩም የይዞታ ማረጋገጫ ካርታው ሲዘጋጅ በ1988 በተነሳው መልከዐ ምድራዊ የመረጃ ሥርዓት /ጂ አይ ኤስ/ መሠረት መሆኑን አብራርተዋል። በአካል የተካሄደ ልኬት ከመልከዐ ምድራዊ የመረጃ ሥርዓት /ጂ አይ ኤስ/ ጋር በማነጻጸር የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ እንደሚሰራ የገለጹት አቶ ክብሮም እነ ወይዘሮ ወርቅዬ ደበላ የተዘጋጀላቸው ካርታ በንጽጽር /ፕሮፖርሽን/ ቤቱ ያረፈበት 24 ካሬ ሜትር እና የግቢው ስፋት ደግሞ 80 ካሬ ሜትር በድምሩ 104 ካሬ ሜትር ነው ብለዋል። "ይህንን ካርታ ተስማምተው ፈርመው ወስደዋል ዛሬ ላይ ለምን ጥያቄ እንደፈጠረባችው አልገባኝም" ሲሉ ምላሽ የሰጡት ኃላፊው በወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ዘመን ትርፍ የከተማ መኖሪያ ቤቶች በአዋጅ ሲወረሱ በእነ ወርቅዬ ደበላ ግቢ ውስጥ የነበሩ ሁለት ትርፍ ቤቶች መወረሳቸውን የግል ማህደራቸው እንደሚያሳይ ጠቁመዋል። በዚህ መሰትም ከ1988 በኋላ የተሰበሰበው የጂአይኤስ መረጃ የሚያሳየው ሶስት ቤቶች እንደሆነ ይገልጻሉ። ''በወረቀት ላይ የተጻፈው መሬት ላይ ሲለካ ካልተገኘ ከየትም መጥቶ ሊሰጥ አይችልም'' ያሉት አቶ ክብሮም ባለይዞታዎቹ እውነታውን መቀበል እንዳለባቸው ተናግረዋል። ቅሬታ አቅራቢዋ ወይዘሮ ወርቅዬ ደበላ ይዞታቸው ላይ የቀበሌ መኖሪያ ቤት መሰራቱን አስመልክቶ ያቀረቡት ቅሬታ በተመለከተ በግለሰቧ ይዞታ ላይ ምንም ዓይነት የቀበሌ ቤት እንዳልተሰራ ገልጸዋል። ቀደም ሲል በልኬትና በሰነድ ተብሎ የሚከፋፈል አሰራር በህብረተሰቡ ዘንድ ውዝግብ እንደፈጠረ የገለጹት አቶ ክብሮም በአሁኑ ወቅት ይህን አሰራር በማስቀረት በሰነድ ላይ የሚገኝ መረጃን ብቻ መሠረት በማድረግ እየተሰራ እንደሆነ ጠቁመዋል። ''ቅሬታ አቅራቢዋ የሚኖሩበትን ቤት ማደስም ሆነ ሌሎች ግንባታዎችን መስራት አልቻልኩም'' ብለው ላቀረቡት አቤቱታ ቦታውን ከሚጋሯቸው ነዋሪዎች ጋር በስምምነት የመሥራት መብት እንዳላቸው ተናግዋል። ከመኖሪያ ቤት እድሳትና ከፍሳሽ ማስወገጃ ጋር በተያያዘ ለቀረበው አቤቱታ በየካ ክፍለ ከተማ የወረዳ 7 የግንባታ ፈቃድ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ማንአይቶት በየነ "አለመኖሬን ማስተላለፍ ትችላላችሁ" በማለት ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም