የደቡብ ክልል አዲሱ አመራር የግጭት ምንጮችን በመለየት አስቸኳይ መፍትሄ ሊሰጥ ይገባል.... የሚዛንና ሆሳዕና ከተማ ነዋሪዎች

69
ሚዛን/ሀሳዕና ሀምሌ 19/2010 በደቡብ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋሉ ግጭቶችና አለመግባባት ምንጮችን በመለየት አስቸኳይ መፍትሄ በመስጠት በኩል አዲሱ የክልሉ አመራር ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ አስተያየታቸውን የሰጡ የሚዛንና ሆሳዕና ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡ የሚዛን አማን ከተማ ነዋሪ አቶ ስለሺ ሞላ ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋሉ ግጭቶች እንዳይስፋፉ ርዕሰ መስተዳድሩና ሌሎች አዲስ ተሿሚ ካቢኔዎች በትኩረት ሊሰሩ ይገባል። " ግጭት በሚስተዋልባቸው አካባቢዎች ፈጥኖ በመድረስ ምንጫቸውን ማጤንና ተገቢ ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል " ብለዋል፡፡ ግጭት እንዲፈጠር የሚፈልጉና የሚያባብሱ ግለሰቦችን ከሕብረተሰቡ በመለየት እርምጃ መውሰድ እንደሚገባም አቶ ስለሺ ተናግረዋል። አቶ ጥላሁን ቢኒያም የተባሉ ሌላው የከተማዋ ነዋሪ በበኩላቸው አብዛኞቹ የክልሉ አካባቢዎች የሚካሄዱ እንቅስቃሴዎች ወጣቶችን ማዕከል ያደረጉ በመሆናቸው የወጣቱን ፍላጎት በመለየት መመለስ እንደሚገባ ገልፀዋል ። እንደ አገር የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠል የታችኛው አመራር በንቃት መስራት እንዳለበት የገለጹት ደግሞ አቶ ጀርናል ኩይ ናቸው፡፡ አዲሱ የክልሉ አመራርም የቅሬታ ምንጭ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በልዩ ትኩረት መስራት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡ በተመሳሳይ የሆሳዕና መምህራን ትምህርት ኮሌጅ መምህር አቶ መንበሩ አበጀ እንዳሉት በክልሉ የአመራር ለውጥ መደረጉ እንደ አገር የተጀመረውን እንቅስቃሴ የሚደግፍ ነው፡፡ "በክልሉ የተከሰተውን አለመረጋጋት ለመመለስ አመራሮቹ ሰፊ ሥራ ይጠበቃቸዋል" ብለዋል፡፡ አዲሱ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደርም የህዝቡን ጥያቄ ሊመልስ የሚችል አመራር ይሰጣሉ የሚል ተስፋ እንዳላቸው ነው የገለጹት፡፡ "ክልሉ የበርካታ ብሔሮችና ብሔረሰቦች መገኛ በመሆኑ አንድነትን የሚያጠናክር እንጂ ዘረኝነትን የሚያራምድ አስተሳሰብ በማስወገድ ክልሉን ወደ ቀደሞ ሰላሙ መመለስ ያስፈልጋል" ብለዋል፡፡ አቶ ተስፋይ መኔቦ የተባሉ የሆሳዕና ከተማ ነዋሪ በበኩላቻው በክልሉ የአመራር ለውጥ መደረጉ ተገቢ መሆኑን ገልጸው አዳዲሶቹ አመራር በተለይ ርዕሰ መስተዳድሩ በርካታ ሥራ እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል፡፡                    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም