በደሃና ወረዳ ከ120 ሚሊየን ብር በላይ ወጭ የተገነባ የመጠጥ ውሀ ፕሮጀክት የምረቃ ስነ ስርአት እየተካሄደ ነው

129

ሰቆጣ፣ የካቲት 8/2013 ( ኢዜአ ) በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር በደሃና ወረዳ ከ120 ሚሊየን ብር በላይ ወጭ የተገነባ የአምደወርቅ ዘላቂ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት የምረቃ ስነ ስርአት እየተካሄደ ነው።

በንጹህ መጠጥ ውሀ ፕሮጀክት ምረቃ ስነ ስርአት ላይ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ፋንታ ማንደፍሮን ጨምሮ ሌሎች  ከፍተኛ አመራሮችና የስራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል ።

የብሄረሰብ አስተዳደሩ ዋና አስተዳዳሪ አቶ በሪሁን ኪዳነ ማርያም በወቅቱ ለኢዜአ እንደገለጹት የንጹህ መጠጥ የውሃ ፕሮጀክቱ ግንባታ ስራ ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ ሲካሄድ ቆይቷል።

የውሃ  ተቋሙ ግንባታ በዋን ዋሽ ፕሮጀክትና በክልሉ መንግስት  በተመደበ  ከ120 ሚሊየን ብር በላይ ወጭ የተደረገበት እንደሆነ ተናግረዋል።

የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቱ  ለህብረተሰቡ የቆየ ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥ መሆኑን ተናግረዋል።


ፕሮጀክቱ የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት በተጨማሪ ለአነስተኛ መስኖ ልማት አገልግሎት መስጠት የሚችል እንደሆነ አመልክተዋል ።

ፕሮጀክቱ  ከአምደ ወርቅ ከተማ ባሻገር የጭላ፣ ብርብራ፣ ቢውልና ሽማምዳን ቀበሌ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል።

"የፕሮጀክቱ መገንባት የወረዳውን የንጹህ መጠጥ ወሀ ሽፋን አሁን ካለበት 47 በመቶ ወደ 52 በመቶ ያሳድገዋል" ያሉት ደግሞ የብሄረሰብ አስተዳደሩ ውሃ፣ መስኖና ኢነርጅ ልማት መምሪያ ሃላፊ አቶ ተገኘ መብራቱ ናቸው።

"እንዲሁም የዞኑን የንጹህ መጠጥ ውሀ ሽፋን ከ50 በመቶ ወደ 53 በመቶ ከፍ ያደርገዋል" ብለዋል ።

በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ፋንታ ማንደፍሮ፣ የክልሉ ዋና አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ወርቅ ሰሙ ማሞን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ አመራሮችና የስራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም