የምርምር ስራዎችን ወደ ተግባር ለመቀየር ቅንጅታዊ አሰራር እንደሚያስፈልግ ምሁራን ገለጹ

94

ደሴ፣  የካቲት 7/2013(ኢዜአ) ሃብትና ጉልበት ፈሶባቸው በምሁራን የሚደረጉ ጥናትና ምርምሮች ወደ ተግባር ተቀይረው የህዝብና የሃገር ችግር ፈች እንዲሆኑ ቅንጅታዊ አሰራር እንደሚያስፈልግ ምሁራን ገለጹ።

"የምርምርና ማህበረሰብ ጉድኝት ለኢኮኖሚው እድገት" በሚል መሪ ቃል 9ኛው አገር አቀፍ የጥናትና ምርምር ኮንፈረንስ በወሎ ዩኒቨርሲቲ ተካሒዷል።

ለሁለት ቀናት በተካሔደውና ትላንት በተጠናቀቀው ኮንፈረንስ ላይ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የውሃ ምህንድስናና አስተዳደር መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር አማኑኤል አባተ እንዳሉት በአገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች የተለያዩ ጥናትና ምርምሮች ይካሄዳሉ፡፡

ይሁን እንጂ ከፍተኛ ወጪና ጉልበት ፈሶባቸው ከተሰሩ በኋላ መደርደሪያ ከማሞቅ ውጭ ወደ ተግባር ተቀይረው ህብረተሰቡን ሲያገለግሉ አይታም ብለዋል።

“ይህ ደግሞ ለአገር ውድቀት ከመሆኑም ባለፈ ጥናቱን በሚሰራው አካል ላይ የሞራል ውድቀትና ሌሎች ጥናቶችን እንዳይሰራ መሰናክል እየሆነ ነው”ብለዋል።

በመሆኑም መንግስትና ተቋማቱ ተቀናጅተው ችግር ፈች ጥናትና ምርምሮች ወደ ተግባር በማስገባት የህብረተሰቡ ችግር እንዲፈታ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል።

ሌላው በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር አቶ አደም ፈቶ በበኩላቸው እንደገለጹት አገር የገጠማትን ፖለቲካዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች ለመቅረፍ ጥናትና ምርምሮች የላቀ አስተዋጽኦ አላቸው።

“ምሁራንና ተቋማት በተለያየ ጊዜ የሚሰሯቸው ጥናትና ምርምሮች ተሰሩ ከማለትና ወጪ ከማባከን ባለፈ ወደ ተግባር ባለመቀየራቸው አገር ከእነ ችግሯ እንድትቀጥል አስገድዷታል”ብለዋል።

"በየጊዜው የሚገጥመውን የኑሮ ውድነትና የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለመቅረፍ በጥናት የታገዘ መፍትሄ ወሳኝ ነው” ያሉት አቶ አደም "አለም አቀፍ ባንኮች ለኢኮኖሚው እድገት" የሚል ጥናት ለኮንፈረንሱ ማቅረባቸውን ገልጸዋል፡፡

ዓለም አቀፍ ባንኮች በሀብት፤ እውቀት፤ ገንዘብና በቴክኖሎጅ የበለፀጉ በመሆናቸው ወደ ኢትዮጵያ ቢገቡ የገጠሩን ህብረተሰብ ያማከለ ብድር፤ ኢንቨስትመንትና ሌሎችንም ስለሚያስፋፉ ኢኮኖሚውን ያነቃቁታል የሚል እምነት እንዳላቸው በጥናታቸው አመልክተዋል።

“በከፍተኛ ወጪና ጉልበት የሚሰሩ ጥናትና ምርምሮች ወደ ተግባር አለመግባታቸው በአገር ላይ ከሚያርሰው ኪሳራ በተጨማሪ የምሁራንን የመስራት ፍላጎት እየዘጉ ነው” ያሉት ደግሞ የወሎ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳንስ ኮሌጅ መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ዳንኤል ወልደ ጻዲቅ ናቸው፡፡

የጤና ተቋማትን አገልግሎት ለማሻሻልና የህብረተሰቡን ጤና በመጠበቅ አምራችና አገር ወዳድ ዜጋ ለመፍጠር የተሰሩ የተለያዩ ጥናቶች በከንቱ መቀረታቸው እንደሚያሳዝናቸውም ተናግረዋል፡፡


እርሳቸውም በጤናው ዘርፍ የተለያዩ ጥናቶችን ማድረጋቸውን ጠቁመው "የቲቢ በሽታ ስርጭትና መከላከያዎቹ " በሚል በአጣዬ ሆስፒታል የሰሩትን ጥናትና ምርምር ማቅረባቸውን ገልጸዋል፡፡

ናሙና ከወሰዱት የህብረተሰብ ክፍል መካከል 9 በመቶው በሽታው መገኘቱን ጠቁመው “ምልክቱን የሚያሳዩ ዜጎች ፈጥነው ወደ ጤና ተቋም ካልመጡና በሽታው መከላከል ካልተቻለ ከባድ ወቅት ላይ ነን” ብለዋል፡፡

“አንድ አካባቢ የሚሰሩ ጥናቶች በሌሎች አካባቢዎች መተግበር ሲገባቸው በሌላ ወጭ ተመሳሳይ ጥናት መደረጉም አግባብ ባለመሆኑ ተቋማትና መንግስት በቅንጅት መስራት ይጠበቅባቸዋል” ብለዋል፡፡

የወሎ ዩኒቨርሲቲ ጥናት ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ፋሪስ ኃይሉ በበኩላቸው በዩኒቨርሲቲው የሚሰሩ ጥናቶች ወደ ተግባር እንዲቀየሩ ከመንግስትና ባለድርሻ አካላት ጋር ለመስራት ጥረት እየተደረገ ነው።

ተመሳሳይ ጥናቶች እንዳይሰሩም በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ክትትል እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው፤ የማህበረሰቡ ችግር የሚፈቱት ጥናትና ምርምሮች እየተለዩ በተለያዩ ቋንቋዎች ታትመው ወደ ህብረተሰቡ እንዲደርሱም ጅምር ስራዎች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡


በቅርቡ በኮሮና ቫይረስ መከላል ዙሪያ ፤ የተሻሻለ ዝርያ ስላላቸው ሰብሎች፤ በአንድነትና ሰላምና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ የተሰሩ ጥናትና ምርምሮችን ወደ ስራ ማስገባታቸውን እንደ ማሳያ አንስተዋል፡፡

በኮንፈረንሱ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ ምሁራን፤ አመራሮች፤ ተጋባዥ እንግዶችና ሌሎችም እየተሳተፉ ሲሆን 44 ጥናታዊ ጹህፎች ቀርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም