የወልዲያ ዩኒቨርሲቲ በሚሰጣቸው ማህበራዊ አገልግሎቶች ተጠቃሚ ሆነናል---የአካባቢው ነዋሪዎች

65

ባህር ዳር፣ የካቲት 7/2013(  ኢዜአ ) የወልዲያ ዩኒቨርስቲ በማህበረሰብ አገልግሎት፣ በምርምርና ቴክኖሎጂ በማስፋፋት የሚሰራቸው ስራዎች ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው የወልዲያ ከተማ ነዋሪዎች ገለፁ።

ዩኒቨርስቲው ከመማር ማስተማር ስራው ባለፈ በማህበራዊ አገልግሎት ለህዝቡ ግልጋሎት እየሰጠ ነው ሲሉ የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት ጠቅሰዋል።

የከተማው ነዋሪ አቶ ፍቅሩ ብርሃኔ ለኢዜአ እንዳሉት የወልዲያ ዩኒቨርስቲ የአካባቢውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ በማነቃቃት ትልቅ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።

ከመማር ማስተማር ስራው በተጨማሪ ለአካባቢው ማህበረሰብ የልማት ስራዎችን በመስራት ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ለአብነትም በወልዲያ ከተማ የተቋቋመው የአይሲቲ ማዕከል የረጅም ጊዜ የኢንተርኔት አቅርቦች ችግርን በመፍታት ተገቢውን አገልግሎት እንዲያገኙ እንዳስቻላቸው ጠቅሷል።

ማዕከሉ የማጣቀሻ መፃህፍትን በመጠቀም ከማገዙም ባለፈ ወቅታዊ ሃገር አቀፍና ዓለም አቀፍ መረጃዎችን ያለምንም ችግር ለማግኘት እንዳስቻላቸው ገልፀዋል።

“የወልዲያ ዩኒቨርሲቲ የስራ እድል በመፍጠር፣ መሰረተ ልማት በመገንባትና መሰል የህዝቡን ፍላጎት መሰረት ያደረጉ ልማቶችን በመስራት ለአካባቢው ህዝብ እያገለገለ ነው” ያለው ደግሞ ወጣት ሲራጅ አደም ነው።

ዩኒቨርስቲው ከመምጣቱ ጋር ተያይዞም በርካታ ባንኮች በወልዲያ መከፈታቸውንና የተሻለ የኢኮኖሚ እንቅሰቃሴ መፈጠሩንም አመልክቷል።

በወልዲያ ከተማ ተቋቋመው የአይሲቲ ማዕከልም ቀደም ሲል ይስተዋል የነበረውን የኢንተርኔት አጥረት ሙሉ በሙሉ በመፍታት ተጠቃሚ እንዳደረገውም ተናግሯል።

በወልዲያ ከተማ አስተዳደር የኔት ወርክ ባለሙያ አቶ ጌታቸው ሃይሉ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ባደረገው ከአንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ የአይ ሲቲ ማዕከሉ ከሁለት ወር በፊት ተቋቁሞ ወደ ስራ ገብቷል።

ለማዕከሉ 27 ኮምፒተሮችና ሌሎች አስፈላጊ ቁሳቁሶች ተሟልተው ለወጣቶች አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ጠቅሰው፤ “ከ30 ሺህ በላይ የመማሪያ መጻህፍት ተጭነው ተማሪዎች እንዲጠቀሙ እየተደረገ ይገኛል”ብለዋል።

የወልዲያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አበበ ግርማ በበኩላቸው ዩኒቨርስቲው ከመማር መስተማር ተግባሩ ባለፈ በማህበረሰብ አገልግሎትና በጥናትና ምርምር እንዲሁም በወቅታዊ ጉዳዮች እያገዘ ነው።

በተለይም ባለፈው ዓመትና በዚህ ዓመት በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝና በአንበጣ መንጋ መከላከል ሰፊ እንቅስቃሴ ማድረጉን ተናግረዋል።

የአካባቢው ማህበረሰብ ከዩኒቨርሲቲው ጋር ጥብቅ ግንኙነት ተፈጥሮ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ በቀጣይም የበለጠ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ፕሬዚዳንቱ አስታውቀዋል።

“የአካባቢውን ማህበረሰብ በግብርና፣ በትምህርትና መሰል ዘርፎች ሁለንተናዊ ጠቃሚነት ለማሳደግ ዘርፈ ብዙ ስራዎች እየተሰሩ ነው” ያሉት ደግሞ የዩኒቨርስቲው የማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ሰለሞን አበጋዝ ናቸው።

የምግብ ዋስትና ችግር ባለባቸው 10 ወረዳዎች ድንች፣ ጤፍ፣ ስንዴን ጨምሮ 13 የሰብል ዝርያዎችን በማሻሻል ከአምስት ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን የምርጥ ዘር ተጠቃሚ መድረግ መቻሉን ተናግረዋል።

“አሁንም ለማህበረሰብ አገልግሎት ብቻ 6 ሚሊዮን ብር በጀት ተመድቦ የህዝቡን መሰረታዊ ችግሮች የሚፈቱ ስራዎችን ለመስራት ጥረት እየተደረገ ይገኛል” ብለዋል።

የወልዲያ ዩኒቨርስቲ በአሁኑ ወቅት ከ20 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተማረ እንደሚገኝም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም