የአደዋ ድል ለሀገር ሉአላዊነት መከበር መስዋዕትነት የመክፈልን አስፈላጊነት ያስተምራል-የመከላከያ ሰራዊት አባላት

128

ድሬዳዋ፣ የካቲት 7/2013(ኢዜአ ) የአደዋ ድል ለሀገር ዳር ድንበርና ሉአላዊነት መከበር መስዋዕትነት የመክፈልን አስፈላጊነት ለትውልድ ያስተማረ ደማቅ ታሪክ እንደሆነ የሀገር የመከላከያ ሠራዊት የሰላም ማስከበር ሰልጣኝ የሠራዊት አባላት ገለጹ።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የሁርሶ የኮንቴንጀንት ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ለ13ኛ ጊዜ ለሰላም ማስከበር ተልዕኮ 15ተኛ ሞተራይዝድ ሻለቃ ተመራቂዎች እንደገለጹት የሃገርን ሉአላዊነት ማስከበርና ለዚህም አስፈላጊውን መስዋዕትነት መክፈል ቅድሚያ የሚሰጡት ተግባር ነው።

ከተመራቂዎቹ መካከል አምሳ አለቃ ብሩክታይት ዘለቀ እንደተናገረችው 125ኛው የአደዋ ድል በዓል በተለያዩ ሁነቶች በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል መከበሩ ስለድሉ ማወቅና መማር መነቃቃት ይፈጥራል።

“የአደዋ ድል የኢትዮጵያ ልጆች በሙሉ ከጫፍ እስከ ጫፍ ተባብረውና አንድነትን ፈጥረው መስዋዕትነት በመክፈል አገር ያዳኑበትና እኛም የነሱን ፈለግ ተከትለን የሀገሪቱን ዳር ድንበርና ሉአላዊነት ለትውልድ ለማሻገር ሞራልና ጀግንነትን ያላበሰን ታላቅ ድል ነው” ብላለች።

“የአሁኑ ትውልድ የመተባበርን፣ የህብረትንና የአንድነትን ኃይል ከአደዋ ድል ሊማር ይገባል” ያሉት ደግሞ አስር አለቃ መብራቱ ታምሩ ናቸው፡፡

ከአድዋ ድል በመማር የተከበረች ሀገርን ለትውልድ የማስተላለፍ ኃላፊነት የሁሉም ዜጋ ሊሆን እንደሚገባ አስታውቀዋል።

ሃምሳ አለቃ ይርዳው በላይ በበኩላቸው “ሰለ አደዋ በብዛትና በዓይነት እንደየባህሉና እንደየቋንቋው ለሁሉም ትውልድ ማስተማር ይገባል” ብለዋል፡፡

“የአሁኑ ትውልድም የራሱን ታሪክና ገድል በየመስኩ መስራት አለበት” ያሉት ሃምሳ አለቃ ይርዳው “የመተባበርንና ተከባብሮ የመታዘዝና የማዘዝን ዋጋ ከአደዋ በመማር የሀገራችንን ዕድገት ማስጠበቅ ይገባል” ብለዋል፡፡

አስር አለቃ ታምራት ፊሊጶስ በበኩላቸው የአደዋ ድል በአለም ህዝብ ዘንድ በጀግንነትና በታላቅ አገር ወዳድነት ያስጠራን የአፍሪካ የድል በዓል ጭምር እንደሆነም ተናግረዋል።

“አያቶቻችን በታላቅ መተባበርና መስዋዕትነት ያቆዩዋትን አገር እኛም ከነሱ ታሪክ ተምረን ያለችንን ሀገር ወደ ታላቅ አገርነት ለመለወጥ በሁሉም መስክ መስዋዕትነት መክፈል ይገባናል” ብለዋል፡፡

የሀገር ሉአላዊነትና ዳር ድንበር ለማስከበር ከመቼውም ጊዜ በላይ በፍቅርና በአንድነት ፀንተው እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ 

የሠራዊቱ አባላት ከአደዋ ድል በዓል ሁሉም ዜጋ መማር ያለበት ለሀገር በሁሉም የስራ ዘርፍ መስዋዕትነትን መክፈል እንደሚገባ ተናግረዋል።

በየተሰማራንት መስክ ውጤት በማስመዝገብ የተሻለች፣ የተከበረችና ሉአላዊነቷ የተጠበቀ አገር ለትውልዱ ለማስተላለፍ ከአደዋ ድል በላይ የሚያስተምር ታሪክ እንደሌለም አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም