በነገሌ ከተማ በ170 ሚሊዮን ብር የሚከናወነው አዳሪ ትምህርት ቤት ግንባታ እየተፋጠነ ነው

62

ነገሌ፣ የካቲት 7/2013(ኢዜአ ) በጉጂ ዞን ነገሌ ከተማ 170 ሚሊዮን ብር ዘመናዊ ሁለተኛ ደረጃ የአዳሪ ትምህርት ቤት ግንባታ እየተፋጠነ መሆኑን የዞኑ ትምህርት ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡
የጽህፈት ቤቱ ሀላፊ አቶ ነጋሽ ቡላላ እንደገለጹት በነገሌ ከተማ በግንባታ ሂደት ላይ ያለው ሁለተኛ ደረጃ አዳሪ ትምህርት ቤት ለዞኑ ብቸኛና የመጀመሪያ ነው፡፡

ግንባታውን በ7 ወራት ጊዜ ውስጥ ሰርቶ ለማጠናቀቅ ከኦሮሚያ ኢንጂነሪንግ ህንጻ ተቋራጭ ድርጅት ጋር ስምምነት መፈረሙን ተናግረዋል፡፡

“ትምህርት ቤቱ 24 የመማሪያ ክፍሎች፣ 3 ቤተ መጻህፍት፣ 3 መሰብሰቢያ አዳራሾች፣ የመምህራን የአስተዳደር ቢሮዎችና የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ያካተተ ነው” ብለዋል፡፡

ግንባታው በመጭው ግንቦት ወር 2013 ዓ.ም ተጠናቆ በሚቀጥለው አመት አንድ ሺህ 200 ተማሪዎችን በመቀበል አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምርም ጠቅሰዋል፡፡

አቶ ነጋሽ እንዳሉት የግንባታው ወጭ ሙሉ በሙሉ የአሮሚያ ክልላዊ መንግስት በመደበው 170 ሚሊዮን ብር የሚሸፈን ሲሆን የትምህርት ቤቱም ግንባታ በአሁኑ ወቅት 40 በመቶ መድረሱን ገልጸዋል።

የነገሌ ከተማ ነዋሪ አቶ በለጠ አጥናፉ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ተማሪዎችን ለመርዳት አዳሪ ትምህርት ቤት እንዲሰራ ጥያቄ ሲያቀርቡ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

“ለትምህርት ቤቱ ግንባታ አስፈላጊ የሆነውን ድጋፍ ሁሉ እንዲያደረግ ህዝብን በማስተባበርና በመቀስቀስ የድርሻዬን እወጣለሁ”ብለዋል።

“የነገሌ ከተማ 03 ቀበሌ ነዋሪ አቶ ጥላሁን ከበደ በበኩላቸው ለአመታት ስናቀርብ የነበረው ጥያቄ እየተመለሰ ነው” ብለዋል።

ሆኖም ግንባታው በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ክትትልና ቁጥጥር ሊደረግበት እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም