ሠራዊቱ በአለም ሠላም አስከባሪነት የተጎናጸፈውን ክብርና ዝና አጠናክሮ ይቀጥላል...ሜጀር ጀነራል መሐመድ ተሰማ

80

ድሬዳዋ፤ የካቲት 6/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በአለም ሠላም አስከባሪነት በመሳተፍ የተጎናጸፈውን ታላቅ ክብርና ዝና አጠናክሮ እንደሚቀጥል በኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት የኢንዶክትሪኔሽን  ዳይሬክቶሬት ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጄነራል መሐመድ ተሰማ አስታወቁ።

በመከላከያ ሚኒስቴር ሠላም ማስከበር ማዕከል የሁርሶ የኮንቲንጀንት ማሠልጠኛ  ትምህርት ቤት ለ13ኛ ጊዜ ያሰለጠናቸውን የሠላም አስከባሪ ሠራዊት ዛሬ አስመርቋል።

ሜጀር ጀነራል መሐመድ ተሰማ  በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ወቅት እንደገለጹት፤ የኢፌዴሪ መንግስት በአፍሪካ ሀገራት የሠላም ማስከበር  ተልዕኮውን በብቃት የሚወጡ የሠራዊት አባላትን በማሰማራት ለሰላም ያለው ቁርጠኝነት በተግባር እያረጋገጠ ይገኛል፡፡

ሠራዊቱ በየተሰማራበት ግዳጅና ተልዕኮ ህዝባዊ ወገንተኝነት በመላበስና ገለልተኛነትን በመጎናጸፍ እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ በተባበሩት መንግስታትና በአፍሪካ ተመራጭ ኃይል እንዲሆን ማስቻሉን አስታውቀዋል፡፡

የሠራዊቱ ቁርጠኝነትና አስተማማኝ የግዳጅና አፈጻጸም የታደጋቸውና የዘመተላቸው  ሀገራትህዝቦች ጭምር ሠራዊቱን እንደራሳቸው ወገን እንዲመለከቱት ማስቻሉን  ሜጀር ጄነራል መሐመድ ተናግረዋል፡፡

ይህን ታላቅ ስምና ዝና ለመጠበቅና ለማጠናከር የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ  ይገኛሉ ያሉት ሜጀር ጄኔራሉ፤ የመከላከያ ሠራዊት በአፍሪካና በሌላው አለም አደባባይ  የሠላም ማስከበር ተልዕኮን ለማጎልበት የሚያስችል የተቀናጁ ተግባራት እያከናወነ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የዛሬ ተመራቂ የሠላም አስከባሪ የሠራዊቱ አባላት ይህንኑ አለም አቀፍ ዝናና ክብር  የበለጠ ከፍ በሚያደርግ መንገድ  መሠልጠናቸውን ጠቁመው፤ የቀሰሙትን እውቀት በመጠቀም ግዳጃቸውን ፈጽመው እንዲመለሱም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የሁርሶ የኮንቴንጀንት ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት ዋና አዛዥ ኮሮኔል ዳኜ በላይ  በበኩላቸው ሰልጣኞቹ ኮሮናን በመከላከልና ሌሎች የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመሻገር  የተጣለባቸውን ተልዕኮ በስኬት መወጣት የሚያስችላቸው ትምህርት እንደተሰጣቸው  ገልጸዋል፡፡

ለሠላም ማስከበር ቅድመ ስምሪት ዝግጁ የሆኑት ተመራቂዎች ከወታደራዊ መሠረታዊያን ሥልጠናዎች በተጓዳኝ አለም አቀፍ የሠላም ማስከበር ስልትና ትምህርት መከታተላቸውን አስረድተዋል፡፡

ይህም የተጣለባቸውን ተልዕኮ ልክ ከነሱ በፊት በተለያዩ ሀገራት እንደተሰማሩት ሌሎቹ  ጓደኞቻቸው በስኬት ለማጠናቀቅ ያስችላቸዋል ብለዋል፡፡  

ከተመራቂዎቹ  መካከል  አስር አለቃ አማረች ደበሌ እንዳሉት፤ በሚሰማሩበት ሀገር  አስተማማኝ ሠላም እንዲሰፍን ከአካባቢው ህብረተሰብ ጋር በመሆን ኃላፊነታቸውን  ለመወጣት ተዘጋጅተዋል፡፡

ሠራዊቱ ያለውን ታላቅ ክብርና ዝና የሚመጥን  ተግባር ለመፈጸመ ዝግጁ መሆናቸውን  ገልጸዋል።

አስር አለቃ መብራቱ ታምሩ በበኩላቸው በሀገርና ሠራዊቱ ላይ ክህደት የፈፀመው የህወሃት ጁንታ በተገረሰሰበት ማግስት አለም አቀፍ የሠላም ማስከበር ተልዕኮ ላይ መሰማራት  ግዳጅን ለመወጣት ይበልጥ ያጠናክራል ብለዋል፡፡

በሥልጠናው ሂደት ግንባር ቀደም እገዛና ድጋፍ ላደረጉ ወታደራዊ መኮንኖችና  ሲቪል ተቋማት ምስጋናና የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል።

ሥልጠና ተከታትለው ለ13ኛ ጊዜ ዛሬ የተመረቁት ወደ ደቡብ ሱዳን-ጁባ የሚዘምቱ  የ15ኛ ሞተራይዝድ ሻለቃ አባላት ናቸው፡፡

በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ላይ የኢፌዴሪ የመከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖችና የድሬዳዋ  አስተዳደር የካቢኔ አባላት ተገኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም