ተመራቂዎች በሰለጠኑበት የሙያ ዘርፍ የአገር ሃብት ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረግ ይጠበቅባቸዋል - ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ

82

የካቲት 6/2013 (ኢዜአ) የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመራቂዎች በሰለጠኑበት የሙያ ዘርፍ የአገሪቷን እምቅ ሃብት ጥቅም ላይ ማዋል እንዳለባቸው የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ አስገነዘቡ፡፡

የአዲግራት ዩኒቨርሲቲ ለስምንተኛ ጊዜ ያሰለጠናቸውን 2 ሺህ 576 ተማሪዎች ዛሬ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ አስመርቋል፡፡

ዶክተር ሳሙኤል ተመራቂዎቹ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን አልፈው ለዚህ ቀን በመብቃታቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡

ተመራቂዎች አገራቸው ከገጠማት የውጭና የውስጥ ጫና እንድትላቀቅ መሥራት እንደሚጠቅባቸውም አሳስበዋል፡፡

የአገሪቷን የተፈጥሮ ሀብት ጥቅም ላይ በማዋል ብልጽግናዋን ለማሳካት እንዲተጉም ነው ሚኒስትሩ ያስገነዘቡት፡፡

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዶክተር ሙሉ ነጋ በበኩላቸው ሠላም ለሁሉም ነገር መሰረት

በመሆኑ ተመራቂዎች ለሰላም ዘብ እንዲቆሙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የአዲግራት ዩኒቨርሲቲ በአጭር ጊዜ ተማሪዎችን መቀበል እንደሚጀምርም ገልጸዋል፡፡

ትምህርታቸውን በአስቸጋሪ ሁኔታ ላጠናቀቁት ተመራቂዎች "የሠላምን ዋጋ ለሌሎች መመስከር አለባችሁ" ብለዋቸዋል፡፡

የአዲግራት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ዛይድ ነጋሽ ዩኒቨርሲቲው በስድስት ኮሌጆችና 46 የትምህርት ክፍሎች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎችን ለምረቃ ማብቃቱን ገልጸዋል፡፡

ከተመራቂዎቹ አንዳንዶቹ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት የነበሩትን ችግሮች አልፈው ለምረቃ በመብቃታቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡

ወደ ሥራ በሚሰማሩበት ወቅት ያስተማራቸውን ማኅበረሰብ በቅንነት እንደሚያገለግሉም እንዲሁ።

የሶስተኛ ትውልድ ዩኒቨርሲቲ የሆነው የአዲግራት ዩኒቨርሲቲ ሥራ የጀመረው በ2004 ዓ.ም ነው፡፡

በምረቃው ሥነ ሥርዓት የአዲግራት ዩኒቨርሲቲ የቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሮ ፍሬነሽ መኩሪያና በርካታ እንግዶች ታድመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም