ከተማ አስተዳደሩ 3 ነጥብ 5 እና ከዛ በላይ ውጤት ያስመዘገቡ ተመራቂዎችን ይቀበላል - ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ

85

የካቲት 6/2013 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ 3 ነጥብ 5 እና ከዚያ በላይ ውጤት ያስመዘገቡ የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ተመራቂዎችን አስተዳደሩ እንደሚቀበላቸው አስታወቁ።

የዩኒቨርስቲው መምህራንም የከተማ አስተዳደሩ ካቢኔ ለመምህራን ባደረገው የቤት አበል ማሻሻያ እንደሚካተቱ ገልጸዋል።

የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ በቀንና በማታው መርሃ-ግብር ያሠለጠናቸውን 2  ሺህ  39  ተማሪዎች በዲፕሎማ፣ በመጀመሪያና  በሁለተኛ ዲግሪ አስመርቋል።

ምክትል ከንቲባ በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ እንዳሉት 3 ነጥብ 5 እና በላይ  ውጤት ያስመዘገቡ  ሁሉንም የ2013 ዓ.ም ተመራቂዎች  የአዲስ አበባ  አስተዳደር  እንደሚቀጥራቸው  ቃል ገብተዋል።

በተጨማሪም የከተማ አስተዳደሩ ካቢኔ ባለፈው ወር ለመምህራን ያስተላለፈው የመኖሪያ ቤት አበል ማሻሻያ የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ መምህራንንም እንዲያካትት ነው ያስታወቁት።

የከተማ አስተዳደሩ ካቢኔ ቀደም ሲል ለመምህራን ይከፈል የነበረውን የቤት አበል ከብር 850 ወደብር 3 ሺህ ብር እንዲሻሻል መወሰኑ ይታወሳል።

ዩኒቨርሲቲው ወደ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ከተሸጋገረ ጀምሮ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በቅርበት እየሠራ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ብርሃነመስቀል ጠና ገልፀዋል።

ከተማ አስተዳደሩን ማገዝ የሚያስችለውን አቅም በምርምር፣ ስልጠናና የማህበራዊ  አገልግሎት ተጠቃሚነት ለማሳደግ ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑንም ተናግረዋል።

ዩኒቨርሲቲው የከተማ አስተዳደሩ ተጠሪ ከሆነ ጀምሮ ከአስተዳደሩ አዲስ  አደረጃጀት  ጋር  ሠፋፊ ተግባራትን አከናውኗል ብለዋል።

በምርምርና ስልጠና እንዲሁም “የኦዲት ባለሙዎች ሳይቀርቡ ማጣራት አይቻልም” የተባለውን የመኖሪያና ኮንደሚኒየም ቤቶች ጉዳይ በማጣራት  የነዋሪዎች  የፍትሃዊነት  ጥያቄ በአጭር ጊዜ እንዲመለስ መደገፉን ጠቅሰዋል።

የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ከተመሰረተ ከ76 ዓመት በላይ ያስቆጠረ ሲሆን ከ80 ሺህ በላይ የተማረ የሰው ሃይል ለአገሪቷ ማበርከቱ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም