ተመራቂዎች የቀሰሙትን እውቀት በመተግበር ለሀገራቸው ኩራትና መመከያ ሊሆኑ ይገባል ዶክተር ኢዮብ ተካልኝ

64

የካቲት 6 /2013 (ኢዜአ) ተማራቂዎች በትምህርት ቆይታቸው የቀሰሙትን እውቀት ሥራ ላይ በማዋል ለሀገራቸው ኩራትና መመኪያ አንዲሆኑ የገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኢዮብ  ጥሪ አቀረቡ።

ወለጋ ዩኒቨርሲቲ ለ15ኛ ጊዜ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሠለጣናቸውን ከ3ሺህ በላይ ተማሪዎችን ዛሬ አስመርቋል ፡፡

የዕለቱ የክብር እንግዳ የገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስትር ዴኤታና የዩኒቨርሲቲ የቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ኢዮብ ተካልኝ እንደተናገሩት ዛሬ ኢትዮጵያ በዕውቀት የበለፀገ፣በምክንያት የሚቃወምና የሚደግፍ ትውልድ ትፈልጋለች።

ለውድ አገሩ እውቀቱንና ጉልበቱን ሊያፈስ የተዘጋጀና ከፊቱ ብሩህ ተስፋ የሰነቀ ትኩስ ኃይልም እንዲሁ።

የዕለቱ ተመራቂዎች የቀሰሙት እውቀት ሥራ ላይ በማዋል ጊዜ የሚጠይቀውን የተለየ ኃላፊነት ተቀብለው ከራሳቸውና ቤተሰቦቻቸው  አልፈው ለሀገራቸው ኩራትና መመኪያ እንዲሆኑ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ሀሰን ዩሱፍ በበኩላቸው ሠልጣኞቹ በቅድመና ድህረ ምረቃ ፕሮግራሞች ትምህርታቸውን የተከታተሉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በተለያዩ የትምህርት መሰኮች ሠልጥነው ዛሬ ከተመረቁት ከ3ሺህ በላይ ተማሪዎችም መካከል 1ሺህ 145 ሴቶች መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡

ከሠለጠኑባቸው የትምህርት መስኮች መካከል እንስሳት ሕክምና፣ጤና ሳይንስ፣ኢንጂነሪንግና ቴክኖሎጂ፣ ተፈጥሮና ኮምፒዩቲሽናል ሳይንስ እንዲሁመ  ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ይገኙበታል።

ዩኒቨርሲቲው በኮሮና ምክንያት ባለፈው ዓመት ትምህርታቸውን ያቋረጡትን ተማሪዎች ዳግም በመጥራትና የማሟያ መርሃ ግብር በማዘጋጀት ለምረቃት ማብቃቱን ዶክተር ሀሰን አብራርተዋል።

ከተመራቂዎቹ መካከል በጋዜጠኝናትና ተግባባት ትምህርት ክፍል ከፍተኛ ነጥብ በማምጣት የሜዳሊያ ተሸላሚው ተካልኝ ከበደ በሰጠው አስተያየት ለትምህርቱ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ለሽልማት መብቃቱን ገልጾ በሠለጠነበት ሙያ ሀገሩንና ህዝቡን ለማገልገል ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል።

ከነርስንግ የትምህርት ክፍል የሜዳለያ ተሸላሚዋ ፌቤን ዲንሳ ጠንክራ በመስራቷ ሜዳሊያ እንዳገኘች ጠቅሳ በተማረችው ሙያ ህብረተሰቡን በቅንነት ለማገልገል እንደምትጥር ገልጻለች። 

ዩኒቨርሲቲው በዕለቱ ለሕብረተሰቡ ከፍተኛ አስተጽኦ ላበረከቱት ለሕንዳዊው ዶክተር ከናን ሀምበላምና  በጡረታ ላይ ለሚገኙት ዶክተር ኤፍሬም ማሞ የእውቅና ምሥክር ወረቀት አበርክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም