ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በዋሽንግተን ዲሲ የሚኖራቸው ቆይታ ስኬታማ እንዲሆን ከተማዋ ድጋፍ ታደርጋለች- ከንቲባ ባውሰር

84
አዲስ አበባ ሀምሌ 19/2010 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በዋሽንግተን ዲሲ የሚኖራቸው ቆይታ ስኬታማ እንዲሆን አስፈላጊውን ድጋፍ ከተማዋ እንደምታደርግ ከንቲባዋ ማውሪን ባውሰር ገለጹ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፊታችን ቅዳሜ ሐምሌ 21 ቀን 2010 ዓም ጀምሮ ለሶሰት ቀናት በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ፣ ሎስ አንጀለስና ሚኒሶታ ከተሞች በመገኘት ለመጀመሪያ ጊዜ በሰሜን አሜሪካ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራ ማህበረሰብ ጋር ይወያያሉ፡፡ በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ካሳ ተክለብርሃን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በአሜሪካ በሚኖራቸው ቆይታ ዙሪያ ትናንት ከዋሽንግተን ዲሲ ከተማ ከንቲባ ማውሪን ባውሰር ጋር መወያየታቸውን በአሜሪካ የሚገኘው  የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስታውቋል። ከንቲባዋ ሚስ ማውሪን ባውሰር ከተማቸው ይህን ታሪካዊ ጉብኝት በማስተናገዷ ደስታ እንደሚሰማቸውና ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዋሽንግተን ዲሲ የሚኖራቸው ቆይታ ስኬታማ እንዲሆን መንግስታቸው አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል። በከተማዋ የሚኖራቸው ቆይታ ውጤታማ መሆን በሚችልበት ማንኛውም መልኩ ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል። ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበረሰብ በዋሺንግተን ዲሲ እንደሚኖሩና እንደሚሰሩ ያስታወሱት አምባሳደር ካሳ በበኩላቸው በዋሺንግተን ዲሲ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የከተማዋ መንግስት እያደረገ ላለው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። አምባሳደር ካሳ ተክለብርሃንና ከንቲባ ሚስ ማውሪን ባውሰር በአዲስ አበባና ዋሽንግተን ዲሲ እህት ከተሞች መካከል ያለው ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ መወያየታቸውን ኤምባሲው አስታውቋል። ሁለቱ ከተሞች የእህትማማችነት ከተማ ስምምነት እ.አ.አ በ2013 መፈራረማቸው ይታወሳል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ሐምሌ 22 ቀን 2010 ዓ.ም  “የጥላቻና የልዩነት ግንብን አፍርሰን የፍቅርና የአንድነት ድልድይ እንገነባለን” በሚል መሪ ሀሳብ በዋልተር ኢ ዋሽንግተን የስብስባ ማዕከል ከኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንደሚወያዩ ኤምባሲው ገልጿል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአሜሪካ በሚኖራቸው ቆይታ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን፥ በአገራቸው እየተካሄደ ላለው ሁለንተናዊ ለውጥ አካል ሆነው ለአገሪቱ ልማትና እድገት አስተዋጽኦ በሚችሉበት ሁኔታ ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉዞ የመንግስት ለመንግስት ግንኙነትን መሰረት ያደረገ እንዳልሆነና በአሜሪካ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር ተገናኝተው መወያየትን ዋና ዓላማ ያደረገ መሆኑም ተገልጿል። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቆይታ ስኬታማ እንዲሆን ከተለያዩ አካላት የተወጣጣ  የዝግጅቱ አስተባባሪ ኮሚቴ ተቋቁሞ የተለያዩ ተግባራት እያከናወነ ነው።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም