የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ሙያዊ ነፃነት ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ ነው- ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ

89

ባህርዳር፣ የካቲት 4/2013 ( ኢዜአ) የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ሙያዊ ነፃነትና ገለልተኛነት ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ ገለጹ።

በከፍተኛ ትምህርት ፖሊሲ፣ በአስር ዓመቱ ስትራቴጅክ እቅድና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ለዘርፉ አካላት የተዘጋጀ ስልጠና በባህርዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።

ሚኒስትሩ ስልጠናውን ሲከፍቱ እንደተናገሩት፤ ስትራቴጅክ እቅዱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ሙያዊ ነፃነትና ገለልተኛነት ለማረጋገጥ ትኩረት ሰጥቷል።

የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ብዙ ቢሰራም በታሰበው ልክ ለውጥ አለመምጣቱን ጠቅሰው፤ ትውልዱን በትምህርት ጥራት፣ ሙያዊ ክህሎትና ስነ ምግባር ማነጽ የወቅቱ አንገብጋቢ አጀንዳ መሆኑን አስረድተዋል።

የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥም የሀገር እድገት ሞተር የሆነውን የመምህራን ልማት በተከታታይነት በማካሄድ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት የአቅም ግንባታ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ ብለዋል።

ለዚህም የመምህራን የኑሮ ደረጃ በማሻሻል ሙሉ ጊዜያቸውን ለመማር ማስተማርና ለምርምር እንዲያውሉ የሚያስችሉ ተግባራትን ማከናወን ይገባል ብለዋል።

የከፍተኛ ትምህርት ፖሊሲና የአስር ዓመቱ ስትራቴጅክ እቅድ ዋና የትኩረት አቅጣጫዎች ለመፈጸምም በዩኒቨርሲቲዎች ዓለም አቀፍ እውቀትና ክህሎት የተላበሰ አመራር መፍጠር አስፈላጊ በመሆኑ ነው።

ኢትዮጵያን በሳይንስና ቴክኖሎጂ ልማት ተወዳዳሪ ለማድረግም ዩኒቨርሲቲዎች ከተለመደው አመራር ዘይቤ በመውጣት ሀገራዊ ግቡን የሚያሳካ ሳይንሳዊ አመራር በየደረጃው መገንባት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

የሚንስቴሩ አማካሪ ፕሮፌሰር ያለው እንዳወቅ የከፍተኛ ትምህርት ፖሊሲ ሰነድን ሲያቀርቡ እንደገለጹት ትምህርት ለአንድ ሀገር ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ብልጽግና ወሳኝ ነው።

ፖሊሲው የተቋማቱን ተልዕኮ የሆነውን መማርና ማስተማር፣ ምርምርና ማህበረሰቡን ያሳተፈ የልማት ስራዎችን ለማከናወን ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር አስረድተዋል።

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ፍሬው ተገኘ በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲውን የጥናትና ምርምር ማዕከል ለማድረግ በተያዘው ግብ  ሰባት ዋና ዋና ፕሮጀክቶች እየተገበሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

የባህር ዳር ከተማ መዋቅራዊ ፕላን በመተግበር፣ ተፈጥሮ ሃብት፣ ዓሳ፣ መስኖና ውሃ ልማት፣ ከህዳሴው ግድብ ጋር ተያይዞ በሚካሄድ የከተማ አመሰራረት እየተተገበሩ ከሚገኙት ፕሮጀክቶች መካከል ጠቅሰዋል።

ፕሮጀክቶቹም የዓለም አቀፍ ዩኒቨርሲቲዎችና ተቋማትን በመሳብ በትብብር የሚካሄዱ በመሆናቸው ሃብት በማመንጨት፣ ተመራማሪዎችን በማሰልጠንና ተሞክሮ በማስገኘት አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ተናግረዋል።

በቀጣይም በሚኒስቴሩ የሚሰጠውን ስልጠና በመጠቀም ዩኒቨርሲቲውን የጥናትና ምርምር ማዕከል ለማድረግ የተጀመረውን እንቅስቃሴ ዳር በማድረስ ሀገራዊ ለውጡን ለማቀላጠፍ እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

ለሶስት ቀናት በሚካሄደው ስልጠና በኢትዮጵያ የሚገኙ የሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ከፍተኛ አመራሮች፣ የሚኒስቴሩ  አመራሮች፣  ባለሙያዎችና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት እየተሳተፉ ነው።

ተሳታፊዎቹ  በከፍተኛ ትምህርት ፖሊሲው ላይ ሰፊ ምክክር፣ ክርክርና ውይይት በማካሄድ መስተካከል ያለበትንና መካተት ያለባቸውን ጉዳዮች ለይተው በማቅረብ የድርሻቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም