የክልሉ ፖሊስ የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎችን ይቅርታ ጠየቀ

90
አሶሳ ሀምሌ 18/2010 የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፖሊስ  በአሶሳ ተከስቶ በነበረው ችግር የከተማዋን ነዋሪዎች ይቅርታ በመጠየቅ ወደ መደበኛ ስራው ተመለሰ፡፡ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን በአሶሳ ከተማ ተከስቶ በነበረው የፀጥታ ችግር ያልተገባ እርምጃ በወሰዱ አንዳንድ  አባላት ምክንያት በፖሊስ ተቋሙ ላይ የተፈጠረውን ቅሬታ ለማስወገድ  ከነዋሪዎች ጋር በመወያየት ህዝቡን ይቅርታ ጠይቋል፡ የከተማዋ ነዋሪዎች በተፈጠረው የፀጥታ ችግር አንዳንድ የክልሉ ፖሊስ አባላት በፈፀሙት ያልተገባ ተግባር በሰው ህይወትና አካል ላይ ጉዳት በመድረሱ ማዘናቸውን  ተናግረዋል፡፡ በፖሊስ ተቋሙ የሚስተዋለው የአቅም ፣የአመለካከትና የስነ-ምግባር ችግር ለጥፋቱ መነሻ በመሆኑ በቀጣይ ተቋሙ ራሱን እንዲያርም ነዋሪዎቹ በማሳሰብ ስህተቱን በይቅርታ ማለፋቸውን ገልፀዋል፡፡ ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ ሃሰን ኢረና በሰጡት አስተያየት  በፖሊስ አባላት የተፈፀመው ስህተት በተቋሙ ላይ እምነት የሚያሳጣ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ በጥፋት ተግባሩ ተሳትፈው ከተያዙት በተጨማሪ መጠየቅ ያለባቸው  አባላት መኖራቸውንም ጠቁመዋል፡፡ ፖሊሳዊ ስነምግባር የጎደላቸው በርካታ አባላት ስላሉ ተቋሙ  ሊያጠራ እንደሚገባ ጠቅሰው ፖሊስ ራሱን ለማረም ይቅርታ መጠየቁ መልካም መሆኑን  ተናግረዋል፡፡ የፖሊስን የይቅርታ ጥያቄ መቀበሉን የገለፀው ሌላው የከተማዋ ነዋሪ ወጣት ሽመልስ ገናናው በበኩሉ " ችግሩ እንዳይደገም በትኩረት ሊሰራ ይገባል "ብሏል፡፡ በፖሊስ አባላት አድሏዊ አሰራር በመኖሩ በቀጣይ ተቋሙ ይህንን  ሊፈትሽ እንደሚገባም ጠቁማል፡፡ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ኮማንደር ነጋ ጃራ በአሶሳ ከተማ ተፈጥሮ በነበረው የፀጥታ ችግር አንዳንድ የፖሊስ አባላት የወሰዱት ያልተገባ እርምጃ ህዝቡን ያስቆጣና ያስቀየመ ተግባር መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ኮማንደር ነጋ እንዳሉት ኮሚሽኑ በጥፋት ተግባሩ የተሳተፉ አባላትና ግለሰቦችን በመያዝ ጉዳያቸው እየተጣራ ነው ብለዋል፡፡ የከተማዋ ነዋሪዎች ለተቋሙ ለሰጡት ይቅርታ ምስጋናቸውን በማቅረብ በውይይቱ ከህዝቡ የተገኙ ሀሳቦችን በግብአትነት  በመቀበል ማስተካከያ እንደሚደረግ አስታውቀዋል፡፡ በፀጥታ ችግሩ ተሳትፈው ያልተጠየቁ የፖሊስ አባላት መኖራቸውን ህዝቡ በገለፀው መሰረት የማጣራት ስራው እንደሚቀጥልና የአባላትን አቅም ለማሳደግ የስልጠና መርሃ ግብሮች እንደሚመቻቹም ጠቁመዋል፡፡ " የፖሊስ አባላት ሙያዊ ስነምግባራቸውን ጠብቀው መስራታቸውን ለማረጋገጥ የክትትል ስርዓቱ የተጠናከረ ይሆናል "ብለዋል፡፡ የከተማው  ነዋሪዎች  በሰጣቸው ይቅርታ መሰረትም ከዛሬ ጀምሮ ወደ መደበኛ ስራቸው መመለሳቸውን አስታውቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም