ኮሌጆቹ በመጪው እሁድ ከስድስት ሺህ በላይ ተማሪዎችን ያስመርቃሉ

60

አዲስ አበባ፣ የካቲት 3/2013 ( ኢዜአ) በአዲስ አበባ የሚገኙ 14 የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ኮሌጆች በመጪው እሁድ ከስድስት ሺህ በላይ ተማሪዎችን እንደሚያስመርቁ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኤጄንሲ አስታወቀ፡፡

የኤጄንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ንጋቱ ዳኛቸው ለኢዜአ እንደጠቆሙት በከተማዋ የሚገኙ ስድስት የፖሊቴክኒክ ኮሌጆችና ስምንት የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኮሌጆች ናቸው ተማሪዎቻቸውን የሚያስመርቁት፡፡

በመጪው እሁድ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ በሚካሄደው የምረቃ ስነ-ስርአት ኮሌጆቹ ያሰለጠኗቸውን 6 ሺህ 800 ተማሪዎች ያስመርቃሉ።

ተማሪዎቹ በ11 የተለያዩ የትምህርት ዘርፎች ከሁለት እስከ አራት ዓመት የሰለጠኑ መሆናቸውን አመልክተዋል።

ተማሪዎቹ ከሰለጠኑባቸው የሙያ መስኮች መካከል ኮንስትራክሽን፣ ጨርቃጨርቅ፣ አውቶሞቲቭ፣ አይሲቲ እና የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ፡፡

ባለፈው ዓመት መመረቅ የነበረባቸው ተማሪዎች በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሳቢያ ቢዘገዩም የማካካሻ ሥልጠና ወስደው በአሁኑ ወቅት ለምረቃ መዘጋጀታቸውን አብራርተዋል፡፡

በተማሪዎች የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ የተለያዩ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ይገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አቶ ንጋቱ ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም