ደባርቅ ዩኒቨርሲቲ የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ የብዝሃ ሕይወት በዘላቂነት ተጠብቆ እንዲለማ በምርምር እያገዘ ነው

113

ጎንደር፣ የካቲት 2/2013 (ኢዜአ) ደባርቅ ዩኒቨርሲቲ በሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ ዘላቂነት ያለው የብዝሃ ሕይወት ጠብቆ ለቱሪዝም ልማት ለማዋል በምርምር እያገዘ መሆኑን አስታወቀ።

የምርምር ሥራው የፓርኩን እምቅ የቱሪዝም የተፈጥሮ ሀብቶችና ተግዳሮቶች ለመለየት እንደሚያስችሉ ተመልክቷል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ተሰማ ዘውዱ ለኢዜአ እንደተናገሩት ምርምሩ የሚካሄደው የፓርኩ አካባቢ ማህበረሰብ ከቱሪዝም ገቢው ይበልጥ ተጠቃሚ ሆኖ ሀብቱን በባለቤትነት እንዲጠብቀው ለማስቻል ነው።

በፓርኩ ውስጥ የሚፈጸሙ ህገ-ወጥ የዱር እንስሳት አደን፣ የእርሻ ስራ ፣ሰደድ እሳትና ልቅ ግጦሽን በዘላቂነት ለማስቀረት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይም ዩኒቨርሲቲው በምርምር እያገዘ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በተለይም በፓርኩ ክልል የሚስተዋለውን የህገ-ወጥ እርሻ መስፋፋት ለመቀነስ አርሶ አደሮች በአማራጭ የገቢ ምንጭ ማስገኛ የልማት ፕሮጀክቶች እንዲሳተፉ የሚያስችሉ ጥናቶች መካሄዳቸውንም ጠቁመዋል፡፡

ፕሮፌሰሩ እንዳሉት በጥናቱ መነሻ መሰረት በፓርኩ ክልል ውስጥ እርሻ የሚያካሂዱ አርሶ አደሮችን በልብስ ስፌት፣ሸክላ ስራና ሽመናና እደ ጥበብ ሙያዎች እንዲሳተፉ በማድረግ አማራጭ ገቢ የሚያገኙበት ሁኔታ እየተመቻቸ ነው፡፡

በፓርኩ አዋሳኝ ወረዳዎች የሚገኙ ነዋሪዎች በፓርኩ ስነ-ምህዳር ላይ በየጊዜው የሚያደርሱትን ጫና ለመቀነስም ምርታማና የተሻሻሉ የሰብል ዝርያዎችን ለማቅረብ የሚያስችሉ አቅጣጫዎች በጥናት መለየታቸውን ተናግረዋል፡፡

በፓርኩ ክልል የሚስተዋለውን ልቅ ግጦሽ ለማስቀረትም አርሶ አደሩ የቤት እንስሳቱን አስሮ በመቀለብና ከብዛት ይልቅ ጥራት ላይ በማተኮር ዝርያቸው የተሻሻሉ የወተት ላሞችን የሚያገኝበትን አሰራር ለመዘርጋት ታቅዷል፡፡

በፓርኩ ላይ የሚከሰቱ የእሳት አደጋዎችን በሳይንሳዊ ዘዴ ለመከላከልና ለመቆጣጠር ባለሙያዎችን ከማሰልጠን ጀምሮ የእሳት አደጋ መከላከያ ግብአቶች የሚሟሉበትን አሰራር በጥናት መለየታቸውም ተመልክቷል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በፓርኩ ክልል የሚያከናውናቸውን የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ፕሮጀክቶች ተፈጻሚ ለማድረግም ከሁለት አለም አቀፍ የልማት ድርጅቶች ጋር በጋራ ለመስራት ስምምነት ማድረጉን ፕሮፌሰር ተሰማ አስረድተዋል፡፡

በበጀት ዓመቱም ዩኒቨርሲቲ በፓርኩና ከፓርኩ ውጪ ለሚያከናውናቸው 35 የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ተግባራት 20 ሚሊዮን ብር መመደቡንም ጠቁመዋል።

የፓርኩን ብዝሃ ህይወትና ስነ-ምህዳር በዘላቂነት ለማስጠበቅ ከዩኒቨርሰቲው ጋር ስምምነት በማድረግ እየሰሩ መሆናቸውን የገለጹት የፓርኩ የህብረተሰብና ቱሪዝም ሃላፊ አቶ ታደሰ ይግዛው ናቸው፡፡

ባለፉት ዓመታት በመንግስት ፣መንግሰታዊ ባልሆኑ ድርጅቶችና ህብረተሰቡ ተሳትፎ በተከናወኑ ተግባራት ፓርኩን አደጋ ውስጥ ካሉ የተፈጥሮ የቅርስ መዝገብ ውስጥ ማውጣት እንደተቻለ ጠቅሰዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው የፓርኩን ብዝሃ ህይወት በማስጠበቅ በኩል ባለፈው ዓመት አስር የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎችን በማስተባበር ሀገር በቀል ችግኞች እንዲተከሉ ማድረጉን አስታውሰዋል፡፡

በፓርኩ ክልል የሚስተዋለውን የልቅ ግጦሽ ለመቀነስና ለማስረቀት እየተደረገ ያለውን ጥረት ዩኒቨርሲቲው በመደገፍ የተለያዩ ተግባራት እያከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ1978 በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት /ዩኔስኮ/ በአለም የተፈጥሮ ቅርስነት የተመዘገበው ፓርኩ 412 ስኩየር ኪሎ ሜትር ስፋት አለው፡፡

የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙትን ዋልያ፣ ቀይ ቀበሮና ጭላዳ ዝንጀሮን ጨምሮ የተለያዩ ብርቅዬ የዱር እንስሳትና አእዋፋት መገኛ ስፍራ እንደሆነም ተመልክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም