አየር መንገዱ ከኦሮሚያ ኅብረት ስራ ባንክ ጋር ስምምነት ተፈራረመ

120

አዲስ አበባ፣ የካቲት 2/2013 ( ኢዜአ) የኢትዮጵያ አየር መንገድና የአየር መንገዱ ቀዳማዊ መሰረታዊ የሰራተኞች ማኅበር ከኦሮሚያ ኅብረት ስራ ባንክ ጋር የብድር ስምምነት ተፈራረሙ።

ስምምነቱ የአየር መንገዱ ሠራተኞች ከባንኩ ለመኖሪያ ቤትና ለተሽከርካሪ መግዣ እንዲሁም ሌሎች ፍላጎቶችን ማሟያ ብድር የሚያስገኝ ነው።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም፣ የኦሮሚያ ኅብረት ስራ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ደርቤ አስፋውና የአየር መንገዱ የቀዳማዊ መሰረታዊ የሠራተኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት ኢንጂነር ተሊላ ደሬሳ ፈርመውታል።

አቶ ተወልደ ከባንኩ ጋር ስምምነቱ የተደረሰው ከሌሎች ባንኮች ጋር ተወዳድሮ መሆኑን ገልፀዋል።

አየር መንገዱ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሳቢያ ሠራተኞቹን ሳይቀንስና ደመወዝ ሳያቋርጥ ማቆየቱን ገልጸዋል።

በወረርሽኙ ሳቢያ ግዙፍ አየር መንገዶች መዘጋታቸውን፣ ቀውስ ውስጥ መግባታቸውንና ሠራተኞቻቸውን ማሰናበታቸውንም አስታውሰዋል።

"አየር መንገዱ የስኬቱ ምንጭ ሠራተኛው ነው ብሎ ያስባል" ያሉት አቶ ተወልደ፤ አቅሙ በፈቀደ መጠን ለሠራተኞቹ ትኩረት እንደሚሰጥ አረጋግጠዋል።

እንደ ዋና ስራ አስፈጻሚው ገለጻ አየር መንገዱ የሠራተኞቹን የቤትና የመጓጓዣ ችግሮች ለመፍታት እየሰራ ነው።

የመኖሪያ ቤት ችግሩን ለመፍታት ባደረገው ጥረት በመጀመሪያ ምዕራፍ 1 ሺህ 200 ቤቶችን ሰርቶ ያስረከበ ሲሆን፤ በሁለተኛው ምዕራፍ 11 ሺህ ቤቶች እያስገነባ ነው ብለዋል።

የቀዳማዊ መሰረታዊ የሠራተኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት ኢንጂነር ተሊላ ደሬሳ በበኩላቸው ስምምነቱ የሠራተኞቹን የመኖሪያ ቤትና የተሽከርካሪ ፍላጎት እንደሚያሟላ ተናግረዋል።

ማኅበሩ ኢትዮጵያ በዓለም ላይ እንድትታወቅ ያደረጉ የአየር መንገዱን ሠራተኞች ጥቅምና መብት ለማስከበር  እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።

ከአየር መንገዱ ጋር በቀጣይም የዲጂታል ባንክ አገልግሎትን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች እንደሚሰራ የተናገሩት ደግሞ የኦሮሚያ ኅብረት ስራ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ደርቤ አስፋው ናቸው።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ 17 ሺህ ሠራተኞች እንዳሉት የተገኘው መረጃ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም