የጢያ ትክል ድንጋይ የእድሳት ሥራ ከሁለት ሳምንት በኋላ እንደሚጠናቀቅ ተገለጸ

193

የካቲት 2 /2013 (ኢዜአ) የጢያ ትክል ድንጋይ የእድሳት ሥራ ከሁለት ሳምንት በኋላ እንደሚጠናቀቅ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ገለጸ።

ባለስልጣኑ የጢያ ትክል ድንጋይ መካነቅርስ ያለበትን ደረጃ ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ዛሬ አስጎብኝቷል።

በባለስልጣኑ የቅርስ ጥገና ባለሙያ አቶ ሀብታሙ አብርሃ በጉብኝቱ ወቅት እንደተናገሩት፤ ቅርሱ ለረጅም ጊዜ ሳይታደስ በመቆየቱ ለቱሪስቶች ምቹ ባለመሆኑ ቅርሱን የማደስ ሥራ እየተከናወነ ነው።

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የቅርሱን ጥገና ለማከናወን የሚያስችል የጥናት ሰነድ ተዘጋጅቶ ወደ ተግባር መገባቱን ገልጸዋል።

የጥገና ሥራውን ለማከናወን 3 ሚሊዮን ብር ወጪ መደረጉን ያመለከቱት ባለሙያው፣ “በጢያ ትክል ድንጋይ መካነቅርስ የነበረውን ሣር የመመንጠር፣ ቦታውን የመደልደል እና አፈሩን በኖራ የማከም ሥራዎች ተከናውነዋል” ብለዋል።

በተጨማሪም ወደ አንድ አቅጣጫ ያጋደሉ ድንጋዮችን የማቃናትና የመትከል ሥራዎች መሰራታቸውን ነው አቶ ሀብታሙ የገለጹት።

ቀደም ሲል ትክል ድንጋዩ ባለበት ቦታ ዝናብ ሲዘንብ ውሃ ያቁር እንደነበረ አስታውሰው፤ በአሁኑ ወቅት የውሃ መውረጃ ቦይ በመሰራቱ ችግሩ መፈታቱን ገልጸዋል።

“የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ መከሰቱን ተከትሎ የጥገና ሥራው ተቋርጦ ነበር” ያሉት ባለሙያው፤ የዕድሳት ሥራው ከሁለት ሳምንት በኋላ እንደሚጠናቀቅ አመልክተዋል።

የጢያ ትክል ድንጋይ መካነቅርስ ከ12 እስከ 14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንደተተከለ መረጃዎች ያሳያሉ።

ስፍራው በ1972 ዓ.ም በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም ቅርስነት መመዝገቡም ይታወቃል።

በተደረጉ ቁፋሮዎች ከትክል ድንጋዮቹ ጀርባ የሰዎች አስክሬን መገኘቱን የባለሙያዎች ጥናት እንደሚያሳዩ በጉብኝቱ ወቅት ተገልጿል።

ድንጋዮቹ የሚተከሉት ለታዋቂ ሰዎችና ዕድሜያቸው ከ18 እስከ 30 ላሉ ወጣቶች እንደነበር ጥናቶች ያሳያሉ።

በደቡብ ክልል ጉራጌ ዞን ሶዶ ወረዳ በሚገኘው የጢያ ትክል ድንጋይ መካነቅርስ ቅጥር ግቢ 41 የቁም ትክል ድንጋዮች የሚገኙ ሲሆን ቁመታቸው እስከ 5 ሜትር ድረስ የሚረዝሙ ድንጋዮች እንዳሉም መረጃዎች ያመለክታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም