ሀገራዊ እና ክልላዊ ምርጫ በደቡብ ክልል በሠላም እንዲጠናቀቅ ዝግጅት እየተደረገ ነው

73

ሀዋሳ ፤የካቲት 2/2013 (ኢዜአ)  ስድስተኛው ሀገራዊ እና ክልላዊ ምርጫ በደቡብ ክልል ሠላማዊ ሆኖ በስኬት እንዲጠናቀቅ ከወዲሁ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ሠላምና ጸጥታ ቢሮ ሃላፊ አቶ አለማየሁ ባውዲ ገለጹ።

ሃላፊው ለኢዜአ እንደተናገሩት ሃገሪቱ የጀመረችውን የለውጥ ጉዞ በጠንካራ መሠረት ላይ ለማቆም ዘላቂ ሠላም በማረጋገጥ ረገድ የጸጥታ ሃይሉ ሚናውን በአግባቡ እንዲወጣ እየተሠራ ነው።

ስድሰተኛው ሃገራዊ እና ክልላዊ ምርጫ በደቡብ ክልል ሠላማዊ እና ዲሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በልዩ ሁኔታ ከወዲሁ ዝግጅት በመደረግ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ከዝግጅቱ መካከል የክልሉ ጸጥታ ሀይሉ በገለልተኝነት ሰላም በማስጠበቅ በትኩረት እንዲሠራ የአቅም ግንባታ ሥልጠና እየተሰጠ መሆኑ ይገኝበታል።

ምርጫውን ስኬታማ ለማድረግም በምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ የሚመራ ሰባት አባላት ያሉት አብይ ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱን አቶ አለማየሁ ጠቅሰዋል።

የክልሉ  ፖሊስ ኮሚሽነር ነቢዩ ኢሳያስ በበኩላቸው የጸጥታ ሃይሉን አቅም በማሳደግ ታላላቅ ሃገራዊ ተልዕኮዎች በብቃት ለመወጣት በሚያስችል መልኩ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ለዚህም በሁለት ዙር 3 ሺህ 256 የልዩ ሃይል አባላት ለሥልጠና መሠማራታቸውን ጠቁመዋል።

ምርጫው ሠላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ እና ነጻ እንዲሆን ለማስቻል ፖሊስ የተጣለበትን ሃላፊነት በብቃት ለመወጣት ቅድመ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም