የመልካቁንጥሬ መካነቅርስን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ አስፈላጊውን መረጃ የያዘ ሰነድ ተልኳል

147

የካቲት 2/2013 (ኢዜአ) የመልካቁንጥሬ መካነቅርስን በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ለማስመዝገብ አስፈላጊውን መረጃ የያዘ ሰነድ መላኩን የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን አስታወቀ።

ባለስልጣኑ በኦሮሚያ እና በደቡብ ክልሎች የሚገኙ ቅርሶች ያሉበትን ሁኔታ፣ የጥበቃና የእንክብካቤ ሥራውን በተመለከተ ከተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ለተውጣጡ ጋዜጠኞች እያስጎበኘ ነው።

ከተጎበኙ ቅርሶች መካከል በኦሮሚያ ክልል አዋሽ መልካ የሚገኘው የመልካቁንጥሬ መካነቅርስ ይገኝበታል።

የመካነቅርሱ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ተሰማ እንዳብራሩት፤ ቦታው ላይ ላለፉት 50 ዓመታት በኢትዮጵያዊያንና በውጭ ተመራማሪዎች ጥናት ሲደረግበት ቆይቷል።

በተለይ በ1975 ዓ.ም በተደረገ ቁፋሮ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዓመተ በላይ ዕድሜ ያስቆጠረ "ሆሞኢሬክተስ" የሚባለው የሰው ዘር በአካባቢው ይኖር እንደነበር የጥናት ግኝት ማመላከቱን አስታውሰዋል።

እንደ አቶ ተስፋዬ ገለፃ፤ በሥፍራው ከ2ሺህ በላይ የተለያዩ የድንጋይ መሳሪያዎች የተገኙ ሲሆን የሰው፣ የጉማሬና የእፅዋት ቅሪተአካላትም እንደተገኙ ነው የገለጹት።

በተጨማሪም በቦታው ላይ ዕድሜው 800ሺህ ዓመት የሚገመት የእንስሳትና የሰው እግር ዳና መገኘቱን አስታውሰው፤ መካነቅርሱን በአግባቡ ማስተዋወቅ ከተቻለ ትልቅ ገቢ ማመንጨት እንደሚችል አስረድተዋል።

ቦታው የድንጋይ ዘመን ቴክኖሎጂዎችን በአንድ ላይ የያዘ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን የዓለም አቀፍ ቅርስ ጥናት ተመራማሪ አቶ ኃይለስላሴ ደስታ ናቸው።

መካነቅርሱ ለጥናትና ምርምር ትልቅ አስተዋፅኦ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዩኔስኮ ከተመዘገበ የሳይንስ ቱሪዝም መዳረሻ መሆን እንደሚችል ተናግረዋል።

በባለስልጣኑ የቅርስ ጥናትና ምርምር ዳይሬክተር አቶ አንዷለም ግርማዬ በበኩላቸው ቅርሱን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ ስለቦታው ዝርዝር የሚገልፅ ሰነድ በቅርቡ ለዩኔስኮ መላኩን አስታውቀዋል።

"በዩኔስኮ በኩል ሰነዱን በማየት እስከቀጣይ ወር መጨረሻ ድረስ ምላሹን ያሳውቃል ተብሎ ይጠበቃል" ያሉት አቶ አንዷለም፤ እስከዛው ድረስ ባለስልጣኑ ቦታውን ዝግጁ የማድረግ ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው የገለጹት።

የመልካቁንጥሬ መካነቅርስ ከአዲስ አበባ በ50 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም