ኢትዮጵያ በቀጣዩ ወር የኮሮናቫይረስ ክትባት ማስገባት ትጀምራለች...ጤና ሚኒስቴር

73

አዲስ አበባ፣ የካቲት 2/2013 ( ኢዜአ) ኢትዮጵያ ከመጋቢት ወር መጨረሻ ጀምሮ የኮሮና ቫይረስ ክትባት ማስገባት እንደምትጀምር የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

የጤና ሚኒስቴር የኮሮና ቫይረስ ክትባትና ቫይረሱን መከላከልን አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ እንዳሉት በቀጣዩ ወር መጨረሻ ዘጠኝ ሚሊዮን የሚሆን ክትባት ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት እየተሰራ ነው።

ባለፉት ሶሰት ወራት ክትባቱን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት የሚያስተባብር ግብረ ሃይል ተቋቁሞ ወደ ስራ መገባቱን አስታውቀዋል።

ክትባቱ መስጠት ሲጀምር አቅመ ደካሞችና ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ቅድሚያ እንደሚሰጣቸው ዶክተር ሊያ ጠቁመዋል።

በተለይ የጤና ባለሙያዎችና ሰራተኞች፣ የጸጥታ አካላትና በትራንስፖርት ዘርፍ የሚሰሩ ሰራተኞችና ሌሎችም ክትባቱን ያገኛሉ ብለዋል።

የክትባት ፍላጎቱ ከፍተኛ ስለሆነ ተጨማሪ ለማግኘት ከአገራት እና ከአፍሪካ ህብረት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።

በአገር አቀፍ ደረጃ የተቋቋመው ግብረ ሃይል የተሳካ የክትባት አሰጣጥና ቁጥጥር እንዲኖር እየሰራ ነው ብለዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት 20 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ክትባቱን እንዲያገኝ ከተለያዩ አጋሮች ጋር  እየተሰራ መሆኑን ዶክተር ሊያ በመግለጫቸው አመልክተዋል።

ለክትባትና ለተያያዥ ወጪዎች 13 ቢሊዮን ብር ወጪ የሚያስፈልግ ሲሆን ይህም ከዓለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች በተገኘ ድጋፍና በኢትዮጵያ መንግስት የሚሸፈን ይሆናል።

ከክትባቱ ውድነትና ተደራሽነት አንጻር ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ክትባቱን መስጠት ስለማይቻል ህብረተሰቡ  መከላከል ላይ ማተኮር አለበት ብለዋል።

በተለይ ከጊዜ ወደ ጊዜ የመሰባሰብና ማስክ ሳያደርጉ መንቀሳቀስ እየተባባሰ መጥቷል ያሉት ዶክተር ሊያ በዚያው ልክ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥርም እየጨመረ መሆኑን በማስታወስ ህብረተሰቡ መከላከል ላይ እንዲያተኩር አሳስበዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ 67 የኮቪድ መከላከያ ክትባቶች ሙከራ ተደርጎ 20ዎቹ የመጨረሻ  ደረጃ ላይ  ደርሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም