የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲና ሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ የመግባቢያ ሰነድ ስምምነት ተፈራረሙ

104

የካቲት1/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲና ሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ ለማኅበራዊ ችግር የተዳረጉ ወገኖች በሚደገፉበት ሁኔታ በጋራ ለመስራት የመግባቢያ ሰነድ ስምምነት ተፈራረሙ።

ስምምነቱን የተፈራረሙት የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊትና የሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ መስራችና ስራ አስኪያጅ ሲስተር ዘቢደር ዘውዴ ናቸው።

የዳያስፖራው ማህበረሰብ በኢትዮጵያ ለሚከወኑ የበጎ አድራጎት ስራዎች ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝና ፍላጎቱም እያደገ መምጣቱን ወይዘሮ ሰላማዊት ገልጸዋል።

ሜሪ ጆይ ኢትዮጵያም በአገር ውስጥ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን የሕብረተሰብ ክፍሎች የመርዳት ተግባር እያከናወነ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

የበጎ አድራጎት ድርጅቱ ከዳያስፖራው ጋር በመስራት ባለው ልምድና በዳያስፖራው ባለው ተቀባይነት እንዲሁም የሚያከናውናቸው ስራዎች አገራዊ ፋይዳ ታይቶ ኤጀንሲው ስምምነቱን መፈራረሙን ጠቁመዋል።

በስምምነቱ አማካኝነት ከዳያስፖራው በሚሰበሰብ ሀብት ሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ ማህበራዊ ችግሮችን ለመቅረፍ ለሚያከናውናቸው ተግባራት ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል።

ኤጀንሲው ከሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ በተጨማሪ በኢትዮጵያ ከሚገኙ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ጋር መስራት እንደሚፈልግም ተናግረዋል።

የሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ መስራችና ስራ አስኪያጅ ሲስተር ዘቢደር ዘውዴ በበኩላቸው ለችግር ተጋላጭ የሆኑ ማህበረሰቦችን የመደገፍ ተግባር መንግስት ብቻውን የሚወጣው ባለመሆኑ የዳያስፖራው ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህ ረገድ በስምምነቱ አማካኝነት በዳያስፖራው ማህበረሰብ ተሳትፎ በትምህርት፣ በጤናና ሌሎች ማህበራዊ ዘርፎች ዜጎችን የሚጠቅሙ ስራዎች እንደሚከናወኑ አመልክተዋል።

እንደዚህ አይነት ስምምነት ዳያስፖራው በበጎ አድራጎት ስራ ላይ በተቀናጀ መልኩ ተሳትፎ እንዲያደርግ ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥርም አክለዋል።

ዳያስፖራው በአገር ውስጥ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራት ላይ እንዲሳተፍ ማስተባበርና ምቹ ሁኔታ መፍጠር የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ከተሰጡት ተግባርና ሃላፊነቶች መካከል የሚጠቀስ ነው።

ሜሪ ጆይ ኢትዮጵያም ከ26 ዓመት በፊት የተቋቋመ የበጎ አድራጎት ድርጅት ሲሆን ለችግር የተጋለጡ ዜጎችን በኢኮኖሚና ማህበራዊ መርሃ ግብሮች ተጠቃሚ ማድረግ ዋነኛ ትኩረቱ አድርጎ እየሰራ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም