የመከላከያ ሰራዊት አባል መሆን አገርንና ሕዝብን ማገልገል ነው - ሌተናል ጄኔራል ባጫ ደበሌ

154

የካቲት 1/2013 (ኢዜአ )የአገር መከላከያ ሰራዊት አባል መሆን አገርንና ሕዝብን ማገልገልና ጀግኖችን መቀላቀል ነው ሲሉ ሌተናል ጄኔራል ባጫ ደበሌ ተናገሩ።

ወጣቶች ወደ ውትድርና ሙያ በመግባት ለሀገርና ሕዝብ ክብር መቆም አለባቸው ብለዋል።

ሌተናል ጄኔራል ባጫ ደበሌ ከመከላከያ ሚዲያ ጋር ባደረጉት ቆይታ የሀገር መከላከያ ሰራዊት በትግራይ ክልል የሕግ ማስከበር እርምጃ ተጋድሎ በመፈጸም ሀገራዊ ተልዕኮውን መወጣቱን ገልጸዋል።

ሰራዊቱ በሕግ ማስከበር እርምጃው የተሰጠውን ተልዕኮ በስኬት በማጠናቀቅ የሀገር አለኝታነቱን ማሳየቱን ተናግረዋል።

ሰራዊቱ በጀግኖች የተሞላ ነው፤ የዚህ ሰራዊት አባል መሆን የጀግኖች አባልና መሪ ከመሆን ባለፈ ክብር የሚያጎናጽፍ ነው ብለዋል።

ማንኛውም ሰው በየትኛውም መስክ ጀግና መሆን ይፈልጋል ያሉት ሌተናል ጄኔራሉ የመከላከያ ሰራዊት አባል መሆን ደግሞ ጀግንነትን የሚያላብስ እንደሆነ አመልክተዋል።

በሰራዊቱ አባል ሆኖ ሕዝብን ማገለግል ትልቅ ክብር መሆኑንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ወጣቶች የውትድር ሙያ ዋና ተግባር ሀገርና ሕዝብን ማገልገል መሆኑን አውቀው ሙያውን እንዲቀላቀሉና የኢትዮጵያ ወታደር የመሆን እድልን እንዲጠቀሙበት ጥሪ አቅርበዋል።

የሀገር መከላከያ ሰራዊት ራሱን ለማዘመን የማሻሻያ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝም መግለጻቸውን ከመከላከያ ዋና ኢንዶክትሪኔሽን ዋና ዳይሬክቶሬት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ሌተናል ጄኔራል ባጫ ደበሌ በትግራይ ክልል በተካሄደው የሕግ ማስከበር እርምጃ በራያ በኩል ያለውን ግንባር ሲመሩ እንደነበር የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም