ለሚጥል ሕመም ያለው የተሳሳተ አመለካከት ሕሙማን ወደ ሕክምና ተቋማት እንዳይሄዱ አድርጓል

82

የካቲት 1/2013 (ኢዜአ) ስለሚጥል ሕመም ያለው የተሳሳተ አመለካከትና የግንዛቤ ማነስ ሕሙማኑ ወደ ሕክምና ተቋማት እንዳይሄዱ ማድረጉን የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

6ተኛው ብሔራዊ የሚጥል ሕመም ሳምንት " በሚጥል ሕመም ለተጎዱ ድምጽ ነኝ" በሚል መሪ ሃሳብ ሲከበር፤ ከየካቲት 1 እስከ 7 ቀን 2013 ዓ.ም ሰፊ የግንዛቤ መፍጠሪያ ንቅናቄ እንደሚካሄድ ተገልጿል።

በዓለም ላይ 50 ሚሊዮን የሚሆኑ ዜጎች በሚጥል ሕመም እንደሚሰቃዩ ጥናቶች ያመላክታሉ።

በኢትዮጵያም ከአንድ ሚሊዮን የሚልቁ ሰዎች የበሽታው ታማሚዎች እንደሆኑ ይታሰባል።

የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው ሕመሙ ካለባቸው ሰዎች ሕክምና የሚያገኙት ከ5 በመቶ አይበልጡም።

የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኤባ አባተም በተሳሳተ ግንዛቤና በልማዳዊ አመለካከቶች አምራች ሊሆኑ የሚችሉ ዜጎች ከሕመሙ ጋር አብረው ይኖራሉ።

በዚህ ሳቢያ "በበሽታው የተያዙ ሰዎች አድልዎና መገለል ሲደርስባቸው ይስተዋላል" ብለዋል።

እንደ ዶክተር ኤባ ገለጻ የሚጥል ሕመም የሕክምና፣ የታማሚውን ቤተሰብና የማኅበረሰቡን ድጋፍ ይጠይቃል።

ድጋፉ ሊተገበር የሚችለው በተለያየ ደረጃ የሚገኘው የኅብረተሰብ ክፍል ስለ ሕመሙ ያለው የተሳሳተ አመላካከትና ግንዛቤ ሲለወጥ መሆኑን ነው የተናገሩት።

በሽታው ተላላፊ አለመሆኑን፣ በእርግማንና በአጉል ልማድ እንደማይመጣና የእምነትና የባህል ሕክምና ምርጫ ማድረግ ላይ ኅብረተሰቡን ማስተማር እንደሚገባም አመልክተዋል።

በቀጣይ የሚመለከታቸው አካላት በሚሰራው የግንዛቤ ማስጨበጫ ላይ በስፋት እንዲሳተፉ ዶክተር ኤባ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ የነርቭ ሐኪሞች ማኅበር ፕሬዚዳንት ዶክተር ሃና ደምሴ በበኩላቸው የሚጥል ሕመም የአዕምሮ ተግባርን በድንገት የሚያውክ ክስተት መሆኑን ተናግረዋል።

እንደ ዶክተር ሃና ገለጻ በአዕምሮ ሕመም ከተያዙ መካከል 70 በመቶዎቹ በቀላሉ መድኃኒት በመውሰድ ሙሉ በሙሉ መዳን እየቻሉ አብዛኞቹ ወደ ጤና ተቋማት አይሄዱም።

"ስለ ሕመሙ ያለው የተሳሳተ አመለካከት ለዚህ ዋነኛው ምክንያት ነው" ብለዋል።

ራስን መሳት፣ ሰውነትን ማንዘፍዘፍ፣ መንቀጥቀጥ፣ መገታተር፣ አረፋ መድፈቅ፣ ምላስን መንከስና መፍዘዝ ከሚጥል ሕመም መገለጫዎች መካከል ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ ከ100 ሺህ ሰዎች 64ቱ በሚጥል ሕመም ይያዛሉ ተብሎ እንደሚታሰብም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ኬር ኤፕለፕሲ ምክትል ኃላፊ አቶ አብይ አስራት ስድስተኛው ብሔራዊ የሚጥል ሕመም ሳምንት "በሚጥል ሕመም ለተጎዱ ድምጽ ነኝ" በሚል መሪ ሃሳብ እንደሚከበር ገልፀዋል።

ስለ ሕመሙ በኅብረተሰቡ ውስጥ ያለውን ግንዛቤ ለማሳደግም ከየካቲት 1 እስከ 7 ቀን 2013 ዓ.ም ሰፊ የንቅናቄ ሥራ እንደሚሰራ ተጠቁሟል።

የግንዛቤውን ቀጣይነት ለማረጋገጥ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ይሰራል ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም