አዲስ ተሿሚ አምባሳደሮች ከዓለም ተለዋዋጭ ሁኔታ ጋር ለመራመድ ራሳቸውን ማዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል

80

የካቲት 1/2013 (ኢዜአ) አዲስ ተሿሚ አምባሳደሮች ከዓለም ተለዋዋጭ ሁኔታ ጋር በመራመድ በየተወከሉበት አገር የኢትዮጵያን ትክክለኛ ገጽታ የማስተዋወቅ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት እንዳለባቸው ተጠቆመ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በተለያዩ አገራት እንዲሰሩ ለተመደቡ አዲስ ተሿሚ አምባሳደሮችና ምክትል ሚሲዮኖች ያዘጋጀው ስልጠና ዛሬ ተጀምሯል።

ስልጠናው በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካና በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ እንዲሁም በአገር ገጽታ ግንባታ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነው።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ አምባሳደሮችና ሚሲዮኖች የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታና ትክክለኛ ገጽታ በየተወከሉባቸው አገራት የማስተዋወቅ ኃላፊነታቸውን በተገቢው መልኩ ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል።

"ከቀጣናዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ተለዋዋጭ ሁኔታዎች ጋር እኩል ለመራመድ ራሳቸውን ማዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል" ብለዋል።

በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ የዜጎችን ጥቅም ከማስከበርና በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ያሉ ጉዳዮችን ከማስረዳት አኳያም ኃፊነት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

አምባሳደሮቹና ምክትል ሚሲዮኖቹ አስፈላጊ የአሰራር ሂደቶች ከተጠናቀቁ በኋላ በቅርቡ ወደተመደቡባቸው አገራት እንደሚያቀኑም አምባሳደር ብርቱካን ጠቁመዋል።

በተለያዩ አገራት ምደባ የተሰጣቸው አምባሳደሮች በበኩላቸው የኢትዮጵያን የሁለትዮሽ ግንኙነት የማጠናከር፣ የዜጎችን ጥቅም የማስከበር፣ በአገር ገጽታ ግንባታና በወቅታዊ ጉዳዮች የሚታዩ የተዛቡ አመለካከቶችን በማረም ትክክለኛውን ሁኔታ የማሳወቅ ሥራ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

ዛሬ የተጀመረው የአምባሳደሮችና የምክትል ሚሲዮኖች ስልጠና እስከ የካቲት12 ቀን 2013 ዓ.ም እንደሚቆይ ታውቋል።

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በቅርቡ ስምንት የባለሙሉ ስልጣን አምባሳደርነትና የአምባሳደርነት ማዕረግ ሹመት መስጠታቸውና የተመደቡባቸው አገራትም ይፋ መደረጉ አይዘነጋም።

በዚሁ መሰረት አምባሳደር ሀደራ አድማሱ-በጋና፣ አምባሳደር ነቢል ማሀዲ-በደቡብ ሱዳን፣ አምባሳደር መላኩ ለገሰ- በሴኔጋል፣ አምባሳደር አደም መሐመድ-በቱርክ፣ አምባሳደር ወይንሸት ታደሰ- በኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ፣ አምባሳደር ደምቢቱ ሐምቢሳ-በጣልያን፣ አምባሳደር ሙክታር ከድር-በአውስትራሊ እና አምባሳደር ሌንጮ ባቲ-በሳዑዲ ዓረቢያ እንዲሰሩ ተመድበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም