ደረቅ ቆሻሻን ብክለትን በማያስከትል መልኩ ማስወገድ የሚያስችል ፕሮጀክት ለአገልግሎት በቃ

61
መቀሌ ሀምሌ 18/2010 ከጤና ተቋማት የሚወገዱ ደረቅ ቆሻሻዎችን የአካባቢ ብክለትን በማያስከትል መልኩ ማስወገድ የሚያስችል አዲስ ፕሮጀክት በመቀሌ ከተማ ተመርቆ ለአገልግሎት በቃ። በጤና ሙያ የተመረቁ አምስት ወጣቶች የፈጠራ ውጤት የሆነው ፕሮጀክት ከከተማዋ ዳርቻ አካባቢ የተገነባ ሲሆን ከጤና ተቋማት የሚወገዱ  ደረቅ ቆሻሻዎችን በአግባቡ ማስወገድ የሚያስችል ነው። አለማትና ቤተልሄም የጤና አጠባበቅ ሥራዎች ማህበር ሥራ ስኪያጅ ወጣት አለማት ኪሮስ ፕሮጀክቱ በተመረቀበት ወቅት እንዳለው፣ የፈጠራ ሥራቸው ደረቅ ቆሻሻዎችን ከአየር ብክለት በጸዳ መልኩ በማቃጠል ማስወገድ ያስችላል። ፕሮጀክቱን ሰርቶ ለአገልግሎት ለማብቃት ከደደቢት ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም የአንድ ሚሊዮን ብር ብድር ማግኘታቸውንም ወጣቱ ተናግሯል። ከእዚህ በተጨማሪ ከቻይና ምግብረሰናይ ድርጅቶች ከ600 ሺህ ብር በላይ ግምት ያለው ዘመናዊ የሕክምና ደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ ተሽከርካሪ ያለቀረጥ በድጋፍ ማግኘታቸውን አስረድቷል። ማህበራቸው በመቀሌ ከተማ ከሚገኙ ከ100 በላይ የመንግስትና የግል የጤና ተቋማትና መድኃኒት ቤቶችጋር ውል በመግባት ቆሻሻቸውን በአግባቡ የማስወገድ ሥራ እንደሚያከናውንም ሥራ አስኪያጁ አስታውቋል። በፕሮጀክቱ የምረቃ ስነ ስርዓት ላይ የተገኙ የትግራይ ክልል ጤና ጥበቃ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሐጎስ ጎደፋይ በበኩላቸው፣ " ፍላጎት ካላ የተለያዩ ፈጠራዎችን በመስራት ራስንና አገርን መጥቅም እንደሚቻል ከፕሮጀክቱ መረዳት ይቻላል" ብለዋል። እንደኃላፊው ገለጻ ፕሮጀክቱ በጤና ተቋማት ውስጥ ጥቅም ላይ የማይውሉ ደረቅ ቆሻሻዎችና መድኃኒቶችን በአካባቢ ላይ ብክለት በማያስከትል ሁኔታ በማቃጠል ለማስወገድ የሚያስችል በመሆኑ በስፋት ጥቅም ላይ እንዲውል ይደረጋል። በቀጣይም በትግራይ ክልል የሚገኙ ከተሞችና ጤና ጽህፈት ቤቶች በወጣቶቹ የፈጠራ ውጤት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ቢሮው ጠንክሮ እንደሚሰራ ዶክተር ሐጎስ ተናግረዋል። በፕሮጀክቱ የምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የግል ጤና ተቋማት ማህበር ተወካይ ዶክተር ኪዳነ እስጢፋኖስ በበኩላቸው፣ ቀደም ሲል ደረቅ ቆሻሻዎችን ማስወገጃ ስፍራ በማጣት ምክንያት ሕብረተሰቡ ለችግር ሲዳረግ መቆየቱን አስታውሰዋል። "በአሁኑ ወቅት በወጣቶቹ የተፈጠረው ፕሮጀክት በየወሩ ተገቢውን ክፍያ በመፈጸም ቆሻሻዎችን በአግባቡ ለማስወገድ መልካም አጋጣሚ ይፈጥራል" ብለዋል። በመቀሌ ከተማ የሄላስ ጥርስ ሕክምና ክሊኒክ ባለቤት ዶክተር ሄለን ነጋሲ በበኩላቸው " በጤና ተቋም ይስተዋል የነበረውን የህክምና ደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ችግር ለመፍታት ፕሮጀክቱ የጎላ ጠቀሜታ አለው " ብለዋል።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም