ኢትዮጵያ እየገነባች ላለው የአረንጓዴ ኢኮኖሚ የፋይናንስ ድጋፍ ያስፈልጋታል--ዶክተር ገመዶ ዳሌ

200
አዲስ አበባ ግንቦት 6/2010 ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት በምታደርገው እንቅስቃሴ የፋይናንስ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋት የአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስትር ዶክተር ገመዶ ዳሌ ገለጹ። ሁለተኛው ዓመታዊ የኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ የሚቋቋም የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ኮንፍረንስ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው። አገሪቷ እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር በ2011 ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ስትራቴጂካዊ እቅድ ማውጣቷ ይታወቃል። በኮፐንሀገኑ ጉባዔ ሀያላን አገሮች ለአየር ንብረት ለውጥ ማጣጣሚያ (አዳፕቴሽን) ሥራ የሚውል በየዓመቱ 20 ቢሊዮን ዶላር ለታዳጊ አገራት ለመስጠት ቃል ቢገቡም እስካሁን እዚህ ግባ የሚባል ድጋፍ አላደረጉም። የአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስትር ዶክተር ገመዶ ዳሌ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በዘላቂ የልማት ግቦች ልትደርስባቸው ያሰበችውን ግብ ለማሳካት የፋይናነስ ድጋፍ ያስፈልጋታል። አገሪቷ ኅብረተሰቡንና ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎችን በማከናውን ለዓለም ምሳሌ ብትሆንም ለዘርፉ ግብ መሳካት ተጨማሪ ድጋፍ ትሻለች ብለዋል። ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት ቀጣይነት ያለው የሰው ኃይል ልማትና ዘመኑ የሚጠይቀውን ቴክኖሎጂ መጠቀም ተገቢ መሆኑን አስረድተዋል። ኢትዮጵያ በ 2030 የካርበን ልቀቷን 64 በመቶ ለመቀነስና ከካርበን ልቀት ነፃ አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት እየሰራች መሆኑንም ገለጸዋል። በአገሪቷ ከፋይናንስና ብቁ የሰው ኃይል እጥረት በተጨማሪ የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ በቂ አለመሆንም ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ግንባታ በምታደርገው እንቅስቃሴ ላይ እንቅፋት መሆኑን አስረድተዋል። የኖርዌይ ዓለም አቀፍ የአካባቢና አየር ንብረት ለውጥ ኢንሼቲቭ ዳይሬክተር ፐር ፍሬድሪክ ኢልሳስ ፓሮ፤ "ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት የምታደርገው ጥረት ለሌሎች አገራት አርዓያ ይሆናል" ብለዋል። የኖርዌይ መንግስትም ይህ የአገሪቷ ጥረት እንዲሳካ በቀጣይም አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም