በትግራይ ክልል የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ላይ ጁንታው ከ240 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ጉዳት አድርሷል

89

አዲስ አበባ፣ ጥር 30/2013 ( ኢዜአ) በትግራይ ክልል የህወሃት ጁንታ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ላይ ባደረሰው ጥፋት ከ240 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት መድረሱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ለ116 ኪሎ ሜትር የኤሌክትሪክ መስመር ጥገና ተደርጎ ስራ መጀመሩን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ገልጿል።

የህወሃት ጁንታ በትግራይ ክልል የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ላይ ባደረሰው ጥፋት ከ240 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ጉዳት መድረሱን ነው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ለኢዜአ የገለጸው።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን እንደገለጹት ጁንታው በክልሉ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ላይ ያደረሰው ጥፋት ከፍተኛ ጉዳትና ኪሳራ አስከትሏል።

በዚህም በክልሉ ከባህርዳር አላማጣ፤ ከኮምቦልቻ አላማጣ እንዲሁም ከተከዜ አክሱምና ከአሸጎዳ መቀሌ በሁለት አቅጣጫዎች የሚገኙ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች መጎዳታቸውን ተናግረዋል።

በሰሜን ሪጅን የሚገኙ ሶስት ባለ 66 ኪሎ ቮልት፣ አምስት ባለ 132 ኪሎ ቮልትና ሰባት ባለ 230 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው አስረድተዋል።

በክልሉ የተለያየ አቅም ያላቸው 1 ሺህ 727 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያላቸው የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ሲኖር በመስመሩ ላይ የተለያየ ጉዳት መድረሱን አስታውቀዋል።

በተጨማሪም ግምቱ 15 ሚሊዮን ብር የሆነ የመለዋወጫ ዕቃ የጫኑ አምስት ተሽከርካሪዎች በጁንታው ተዘርፈው እስካሁን ያሉበት እንደማይታወቅ ገልጸው፤ ይህም በጥገና ስራው ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል ብለዋል።

በወልቃይት በቢሮዎች፣ የሰራተኛ መኖሪያ ቤት የመለዋወጫ ዕቃዎች ማስቀመጫ ክፍሎች ላይ ጉዳት መድረሱንና የተዘረፈውን ጨምሮ ጉዳቱ በገንዘብ እንዳልተተመነ ተናግረዋል።

በማስተላለፊያ መሥመሮችና ሰባት የኃይል ተሸካሚ ማማዎች ላይ ጉዳት መድረሱንም ነው አቶ ሞገስ ያስታወቁት።

ኢትዮ ቴሌኮም የሚጠቀምበት ኦ ፒ ጂ ኤን የተባለ ፋይቨር ላይ የደረሰው ጉዳት ግምት እስካሁን እንዳልወጣም ተናግረዋል።

በጉዳቱ ከ245 ሚሊዮን ኪሎ ዋት በላይ ኃይል መባከኑን ያስረዱት አቶ ሞገስ፤ ኃይሉ ቢሸጥ ከ146 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ይገኝበት ነበር ብለዋል።

በማስተላለፊያ መስመሮች ላይ የሚደረገው የፍተሻ ሥራ ከ80 በመቶ በላይ መድረሱን ጠቁመው የተከዜ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ መስመርን ጠግኖ ከብሄራዊ የኃይል ቋት ጋር የማገናኘትና ወደ መቀሌ የሚሄደው የ230 ኪሎ ቮልት መስመር ጥገና እንደሚከናወንም ገልጸዋል።

በተጨማሪም ከተከዜ ሽሬ አክሱም ካሉት ጥምር የስርጭት መስመሮች ላይ ሁለት መስመሮችን እንዲሁም ከመቀሌ መሆኒ የጥምር ስርጭት መስመር ተጠግነው ወደ ስራ እንደሚገቡ አቶ ሞገስ ተናግረዋል።

በአስቸጋሪ መልክዓ ምድሮችና ሁኔታዎች አልፈው የጥገና ስራ ያከናወኑ ባለሙያዎችን በማመስገን በቅርብ ጊዜ ቀሪ ስራዎች ተጠናቀው አገልግሎቱ ሙሉ በሙሉ እንደሚመለስ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ብዙወርቅ ደምሴም እንዲሁ እስካሁን 116 ኪሎሜትር ያህል የኤሌክትሪክ መስመር ጥገና ተደርጎ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ለኢዜአ ተናግረዋል።

የደረሰው ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ  ሙሉ በሙሉ ጥገና ተደርጎ ወደ ስራ ማስገባት አለመቻሉን ጠቁመው በአሁኑ ወቅት ለህብረተሰቡ መሰረታዊ የሆኑ ፍላጎቶችን ሊመልስ የሚችል የኤሌክትሪክ አገልግሎት መቅረቡንም ገልጸዋል።

መቀሌ ከፍተኛ የኢንዱስትሪ አካባቢ እንደመሆኑ በሁለት መስመር በኩል ሀይል እንደሚገኝ ጠቁመው አንደኛው ትራንስሚሽን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል መጠገኑንና ሁለተኛውን መስመርን ለመጠገን ከፍተኛ ወጪ እንደሚጠይቅ አስረድተዋል።

እስካሁን በተሰራው ስራ አብዛኞቹ የትግራይ ከተሞች የኤሌክትሪክ አቅርቦት ማግኘታቸውን ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚው ገልጸዋል።

ቀሪ ስራዎችን በአጭር ጊዜ ውስጥ አጠናቆ ሙሉ ለሙሉ አገልግሎት ለመስጠት በአገር ውስጥ የማይገኙ እቃዎችን ከውጭ የማስመጣት ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

አሁን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ያላገኙ ከተሞች እነዚህ ስራዎች ሲጠናቀቁ ተጠቃሚ እንደሚሆኑም አስታውቀዋል።

በቀጣይ አገልግሎቱን ወደነበረበት ለመመለስ  329 ኪሎሜትር የሚጠጋ የመልሶ ግንባታ እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።

ይህንንም ለማከናወን 198 ሚሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ነው ያብራሩት።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ መላኩ ታዬ በበኩላቸው የተቋሙ አመራርና ሰራተኞች ባደረጉት ርብርብ ለችግሩ ፈጣን መፍትሄ እየተሰጠ እንደሚገኝና በቀጣይም መስመሩን በማስተካከል ዘለቄታዊ መፍትሔ እንደሚሰጥም ተናግረዋል።

በተከናወነው የጥገና ስራ በመቀሌ ዲስትሪክት ስር የሚገኙ በ25 የአገልግሎት መስጫ ማዕከላት ስር የሚገኙ ብዛት ያላቸው አካባቢዎች የኤሌክትሪክ አገልግሎት አግኝተዋል፡፡

በተከናወኑ የጥገና ስራዎች በኮረም፣ በዓዲሽሁ፣ በኲሓ፣ በዓዲ ጉዶም፣ በውቅሮ፣ በዓዲግራት፣ በአጉላዕ፣ በሳምረ፣ በሓውዜ፣ በዓብይዓዲ፣ በጭላ፣ በብዘት፣ በዕዳጋ ሓሙስ፣ በሃገረሰላም፣ በደውሃን፣ በመኾኒ፣ በአላማጣና በማይጨው አገልግሎት መስጫ ማዕከላት ስር የሚገኙ ከተሞች የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲያገኙ ተደርጓል ብለዋል። 

አቶ መላኩ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በራሱ ወጪና የሰው ኃይል በመጠቀም ባደረገው ሰፊ የመልሶ ግንባታ ሥራ 116 ኪሎ ሜትር የሚሆን የወደመ የዲስትሪቢዩሽን ኔትዎርክ በመጠገን በአሁኑ ወቅት አብዛኞቹ የክልሉ አካባቢዎች የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉን ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም