በጋምቤላ ክልል ህገ-ወጥ እንቅስቃሴዎችን ለመከላከል የጸጥታ አካላት በትኩረት ሊሰሩ ይገባል -አቶ ተንኳይ ጆክ

128

ጋምቤላ፣ ጥር 30/2013(ኢዜአ) በጋምቤላ ክልል ህገ ወጥ የጦር መሰሪያ ዝውውርን ጨምሮ ሌሎች የውስጥና የድንበር ዘለል የጸጥታ ችግሮችን ለመከላከል የጸጥታ አካላት ጠንክረው ሊሰሩ እንደሚገባ የጋምቤላ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተንኳይ ጆክ አሳሰቡ።

በክልሉ ከሚገኙ 13 ወረዳዎች የተመለመሉ ከ800 በላይ የአካባቢ ሚሊሻዎች ከአንድ ወር በላይ የተግባርና የንድፈ ሀሳብ ስልጠና ወሰደው ትናንት ተመርቀዋል።

ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ ተገኝተው እንዳሉት የክልሉ መንግስት በየደረጃው የሚገኙ የጸጥታ መዋቅሮችን በማጠናከር የህግ የበላይነትን በማስጠበቅ የዜጎችን ሰላምና ሰብአዊ መብት ለማረጋገጥ በትኩረት እየሰራ ነው ብለዋል።

በመሆኑም በዕለቱ የተመረቁትን የሚሊሻ አባላት ጨምሮ በየደረጃው የሚገኙ የጸጥታ አካላት ከህዝቡ ጋር በመሆን በክልሉ ያለውን ሰላም በዘላቂነት ለማረጋጥ ጠንክው ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በተለይም ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርን ጨምሮ በክልሉ ጠረፋማ አካባቢዎች የደቡብ ሱዳን የሙርሌ ጎሳ አባላት ሚፈጽመውን ህፃናትን አፍኖ የመውሰድና የቀንድ ከብት ዘረፋ ወንጀሎችን በመከላከል ረገድ ከጸጥታ አካላቱ ከፍተኛ ኃላፊነት እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

“እንዲሁም ድንበር ዘለል የፈላታ አርብቶ አደሮች ህገ-ወጥ ጦር መሳሪያ ዝውውርን ከማስፋፋት ባለፈ በርካታ የቀንድ ከብቶቻቸውን ይዘው በመግባት በኢንቨስትመንት እርሻዎችና በጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክ ላይ ጉዳት ስለሚያደርሱ እንዳይገቡ መከላከል ይገባልም”ብለዋል። 

በዘንደሮው ዓመት የሚካሄደው ስድስተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ ሰላማዊና ፍትሃዊ በሆነ መልኩ እንዲጠናቀቅም የጸጥታ አካላት ከየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ወገንተኛነት በጸዳ መልኩ እንዲሰሩም አሳስበዋል።

የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ቶማስ ቱት በበኩላቸው ሰልጣኝ የሚሊሻ አባላት በቆይታቸው የተሰጣቸውን የተግባርና የንድፈ ሃሳብ ስልጠና በመጠቀም የመጡበትን አካባቢ ህዝብ ሰላም ለማስጠበቅ ጠንክረው መስራት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

የሚሊያሻ አባላቱ በኢታንግ ልዩ ወረዳ በነበራቸው 34 ቀናት የስልጠና ቆይታ በጦር መሳሪያ አጠቃቀምና በሰብአዊ መብት አያያዝ ዙሪያ የተግባርና የንድፍ ሃሳብ ስልጠና እንደተከታተሉም ተገልጿል።

ከስልጠናው ተሳታፊዎች መካከል አቶ ኡሞድ ኡቻላ እንደተናገሩት ከአንድ ወር በዘለለው የስልጠና ቆይታቸው በርካታ የተግባርና የንድፈ ሃሳብ እውቀት ማግኘት ችለዋል።

በመሆኑም ያገኙትን እውቀት በመጠቀም በአካባቢያቸው የሚፈጠሩ የጸጥታ ችግሮችን ለመፍታት እንደሚሰሩም  ገልጸዋል።

ሌላኛዋ የስልጠናው ተሳታፊ ተመራቂ ወይዘሮ አረጋሽ አምባው በሰጡት አስተያየት በስልጠና ቆይታቸው ያገኙትን እውቀት በመጠቀም የአካባቢያቸውን ማህበረሰብ ለማገልገል በቂ ዝግጅት አድርገዋል።

ክልሉ ከደቡብ ሱዳን ጋር የሚያዋስን ድንበር ያለው እንደ መሆኑ ተመራቂዎቹ በድንበር አካባቢ የሚያጋጥመውን ህገ-ወጥ እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር የሚደረገውን እንቅስቃሴም ያግዛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም