የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድን ግንባታ 78 ነጥብ 3 በመቶ ደርሷል ... የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር

57

አዲስ አበባ፤ ጥር 28/2013(ኢዜአ) የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ 78 ነጥብ 3 በመቶ መድረሱን የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ገለጸ።

ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ተቋሙ ያከናወናቸውን ተግባራት በሕዳሴ ግድብ ላይ ትኩረት አድርገው መግለጫ ሰጥተዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ አጠቃላይ ግንባታ፣ የሲቪል ስራ፣ የማሽን ተከላና ሌሎች ስራዎች የደረሱበትን ደረጃ አብራርተዋል።

የግድቡ ግንባታ ባለፈው ሰኔ 2012 ዓ.ም ከነበረበት 74 ነጥብ 02 በመቶ አፈጻም እስከ መጪው ሰኔ 30 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ 81 በመቶ ለማድረስ መታቀዱን ገልፀዋል።

አሁናዊ የግንባታ አፈፃፀሙ 78 ነጥብ 3  ሲሆን 4 ነጥብብ 05 በመቶ እድገት ማሳየቱን ተናግረዋል። 

እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ ይህ የእድገት ጭማሪ በሕዳሴ ግድብ አሰራር ፈጣን የሚባል ሲሆን የሲቪል ስራውም 91 በመቶ ተጠናቋል ነው ያሉት። 

በቀሪዎቹ ወራት ሁለተኛውን የውሃ ሙሌት ለማሳካት ርብርብ እንደሚደረግም ሚኒስትሩ ገልፀው፤ ሃይል ከሚያመነጩ 13 ተርባይኖች ሁለቱ ቅድመ ማመንጫዎች በመጪው ክረምት ማምረት እንደሚጀምሩም ገልጸዋል።

ለዚህም የኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራውና የተርባይን ገጠማው እየተከናወነ መሆኑን ገልጸው፤ ይህን ለማሳካት ርብርብ እየተደረገ ነው ብለዋል።

ግድቡ ውሃ እንዲሞላ የብረት ስራዎችና የተርባይን ተከላ ተግባራት ወሳኝ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

ሚኒስትሩ የግድቡ አጠቃላይ ግንባታ በታቀደው መንገድ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸው በግድቡ ዙሪያ የሚካሄዱ ድርድሮችን አስመልክተውም ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም