ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን አሜሪካ ከአፍሪካ ጋር ያላትን ግንኙነት እንደምታጠናክር ተናገሩ

98

ጥር 28/2013 (ኢዜአ) አሜሪካ ዓለም አቀፍና አህጉራዊ በሆኑ አጀንዳዎች ከአፍሪካ ጋር በጋራ ለመሥራት ቁርጠኛ መሆኗን አዲሱ የአገሪቷ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ተናገሩ።

ፕሬዚዳንቱ ነገና ከነገ በስትያ የሚካሄደውን 34ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ስብሰባ አስመልክተው በበይነ መረብ የቪዲዮ መልዕታቸውን አስተላልፈዋል።

ፕሬዚዳንት ባይደን በመልዕክታቸው ያለፈው የፈረንጆች ዓመት ዓለም ምን ያህል እርስ በእርስ እንደተሳሰረችና አንድ መሆኗን ለመመልከት ችያለሁ ብለዋል።

የዓለም ሕዝቦች ዕጣ ፈንታም እርስ በእርሱ የተሰናሰነ መሆኑን መገንዘባቸውን ገልጸዋል።

በዚህም የተነሳ እርሳቸው የሚመሩት የአሜሪካ አስተዳደር ከዓለም አገራትና ዓለም አቀፍ ቋማት ጋር በጋራ ለመሥራት ቁርጠኛ መሆኑን ነው ያረጋገጡት።

ከነዚህም ዓለም አቀፍ ተቋማት መካከል የአፍሪካ ኅብረት አንዱ መሆኑን ጠቁመው፤ አስተዳደራቸው ከኅብረቱ ጋር ያለውን ግንኙነት እንደሚያጠናክር አክለዋል።  

በዚህም የጋራ የሆነውን ራዕይ በማሳካት መጪውን ጊዜ የተሻለ ማደረግ እንደሚቻል ተናግረዋል።  

በመጪው ጊዜ ለንግድና ኢንቨስትመንት ትኩረት በመስጠት የጋራ ብልጽግናን እውን ማድረግ እንደሚቻል ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል።

በተለይም በሠላምና ደኅንነት፣ በዴሞክራሲ ተቋማት ግንባታ፣ በሠብዓዊ መብትና በሌሎችም ጉዳዮች ስኬት ሊመዘገብ እንደሚገባ ነው ያመለከቱት።

ሴቶች፣ ህጻናትና አካል ጉዳተኞች እንዲሁም ሌሎች የማኅበረሰበ ክፍሎችን አካታች የሆኑ ሥርዓቶች መዘርጋት እንደሚገባም ገልጸዋል።

እነዚህንም ለማሳካት ከፊትለፊት የሚገጥሙ ችግሮችን መጋፈጥ ይገባል ያሉት ፕሬዚዳንት ባይደን በተለይም ኮቪድ-19ን መከላከል ትኩረት ይፈልጋል ብለዋል።

ያም ብቻ ሳይሆን በቀጣይ ዓለም የሚገጥሟትን የጤና ችግሮች ለመቋቋም የአቅም ግንባታ ችላ ሊባል የማይገባው ገዳይ መሆኑን አንስተዋል።   

በዚህም ከአፍሪካ ኅብረት የበሽታ መከላከል ማዕከል ሲ.ዲ.ሲ ጋር በመሆን የጤና ደህንነትን ለማረጋገጥ አሜሪካ በጋራ እንደምትሰራ ገልጸዋል።

ከአፍሪካ ኅብረት ጋር በአየር ንብረት ለውጥ መከላከልና በአህጉሪቷ የበርካታ ሰዎችን ህይወት የሚቀጥፈውን ግጭት ለማስቆም በጋራ እንሰራለን ብለዋል።

ፕሬዚደንት ባይደን እነዚህን ግቦች እውን ለማድረግ አሜሪካ ከአፍሪካ ኅብረት ጋር አጋርነቷን በማጠናከር ውጤታማ ሥራ ለመሥራት ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል።     

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም