ኮቪድ-19 ካንሰርን ጨምሮ ለሌሎች ተላላፊ በሽታዎች የሚሰጠው ትኩረት እንዲቀንስ አድርጓል

68

አዲስ አበባ፣ ጥር 26 /2013 (ኢዜአ)  የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ካንሰርን ጨምሮ ሌሎች ተላላፊ በሽታዎች አነስተኛ ትኩረት እንዲሰጣቸው ማድረጉን ማቲዎስ ወንዱ - የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ አስታወቀ።

በኢትዮጵያ የካንሰር ታካሚዎች ወደ ጤና ጣቢያ ሄዶ የመመርመር ፍላጎታቸው ዝቅተኛ እንደሆነም አመልክቷል።

22ኛው የዓለም የካንሰር ቀን በኢትዮጵያ "እያንዳንዳችን በጋራ የምናደርጋቸው ተግባራት ካንሰርን ለመከላከል ወሳኝ ናቸው" በሚል መሪ ሃሳብ ነገ ለ14ኛ ጊዜ ይከበራል።

ማቲዎስ ወንዱ - የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ የካንሰር ህመም ሰዎችን በከፍተኛ ሁኔታ እያሰቃየና ለሞት እየዳረገ እንደሚገኝ የዓለም የካንሰር ቀንን አስመልክቶ ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

ሕመሙ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስርጭቱ እያደገ መምጣቱንና በኢትዮጵያም በሕመሙ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን አመልክቷል።

በኢትዮጵያ ስለ ሕመሙ ያለው ግንዛቤና የካንሰር ታካሚዎችም ወደ ጤና ተቋም ሄዶ የመመርመር ፍላጎታቸው ዝቅተኛ እንደሆነ ገልጿል።

የካንሰር ታካሚዎች ዘግይተው ወደ ሕክምና መምጣታቸው፣ በቂ የሕክምና ማዕከላት ተደራሽ አለመሆናቸው፣ የተመቻቸና ደረጃውን የጠበቀ የመመርመሪያ መሳሪያ እንዲሁም መድሐኒቶች በቀላሉና በተመጣጣኝ ዋጋ አለመገኘታቸው ከሕመሙ ታክሞ መዳንን ፈታኝ አድርጎታል ብሏል ሶሳይቲው።

አብዛኞቹ የካንሰር ታካሚዎች ወደ ጤና ተቋም ዘግይተው እንደሚመጡና ይህም የሕክምና ውጤታቸው አመርቂ እንዳይሆን እንደሚያደርግ፤ የመዳን እድላቸውንም እንደሚቀንስ አመልክቷል።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወደ ኢትዮጵያ መግባት የካንሰር ሕመምተኞችን በመርዳት ላይ የተሰማሩ ተቋማትን ስራ ይበልጥ ፈታኝ አድርጎታል ብሏል።

ወረርሽኙ ለካንሰርና ሌሎች ተላላፊ ያልሆኑ ሕመሞች የሚሰጣቸውን ትኩረት አነስተኛ እንዳደረገው የካንሰር ሶሳይቲው አስታውቋል።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የካንሰር ታማሚዎች በቤታቸው እንዲወሰኑ፣ በወቅቱ ወደ ሕክምና ተቋማት ሄደው መታከም እንዳይችሉ፣ የሕክምና ቀጠሯቸውን እንዲያራዝሙና እንዲሰርዙ በማድረግ ተጽእኖ እያደረሰ እንደሚገኝ ገልጿል።

ወረርሽኙ የካንሰር ሕሙማን ከጤና ባለሙያዎች ማግኘት ያለባቸውን የምክር አገልግሎት እንዳያገኙ ከማድረጉ በላይ በታማሚዎች ላይ የስነልቦና ጫና እየፈጠረባቸው እንደሚገኝና ይህም ለተጨማሪ የጤና እክል ሊዳርግ እንደሚችል አመለክቷል።

በዚህ አስቸጋሪና የሁሉንም የጋራ ርብርብ በሚጠይቅ ወቅት ለካንሰር ሕሙማን ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ድጋፍና ማድረግ አጋርነትን ማሳየት እንደሚጠይቅም አስታውቋል።

ግለሰቦች፣ የጤና ተቋማት፣ ማህበራት፣ አጋር አካላትና መገናኛ ብዙሃን በጋራ በመሆን ማህበረሰቡ ስለ ካንሰር ያለውን ግንዛቤ የማሳደግ ሃላፊነታቸውን በመወጣት ካንሰርን ለመከላከል፣ የሕሙማንን ስቃይ ለመቀነስና ሕይወት ለማትረፍ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርቧል።

ሶሳይቲው ራሳቸውን ግንባር ቀደም ተሰላፊ አድርገው ለሚሰሩ የጤና ባለሙያዎች፣ ነርሶች፣ ሐኪሞች፣ በጎ ፈቃደኞችና ሌሎች ድጋፍ የሚያደርጉ ተባባሪ አካላት ሶሳይቲው ምስጋና አቅርቧል።

ዓለም አቀፍ የካንሰር ቀን የካንሰር ሕሙማን በማሰብና የጤና ባለሙያዎችን በመዘከር እንደሚከበር የካንሰር ሶሳይቲው ገልጿል።

እ.አ.አ በ2000 በፈረንሳይ መዲና ፓሪስ ካንሰርን ለመከላከል በተዘጋጀ ዓለም አቀፍ ጉባኤ የዓለም የካንሰር ቀን እንዲከበር በተወሰነው መሰረት ቀኑ በየዓመቱ ጥር 27 ታስቦ ይውላል።

ጤናማ ያልሆነ አመጋገብ፣ ከልክ ያለፈ ውፍረት፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ፣ ሲጋራ ማጤስና አልኮል መጠጣት ለካንሰር ሕመም ስርጭትና ሞት መስፋፋት ዋነኞቹ ምክንያቶች ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም