በሕገወጥ መንገድ ተይዘው የነበሩ 139 ቤቶች በችግር ውስጥ ለሚገኙና ለአቅመ ደካሞች ተላለፉ

70

አዲስ አበባ፣ ጥር 26 /2013 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ የአራዳ ክፍለከተማ በሕገወጥ መንገድ ተይዘው የነበሩ 139 ቤቶችን በችግር ውስጥ ለሚገኙና ለአቅመ ደካሞች አስረከበ፡፡

የቤቶቹን ቁልፎች ያስረከቡት ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ የለውጥ አመራሩ ስራ ሲጀመር ቃል ከገባቸው ጉዳዮች የኅብረተሰቡን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ አንዱ እንደሆነ አስታውሰዋል፡፡

በርካቶች የዕለት ጉርስ ባጡባት ከተማ ስግብግብ ግለሰቦች በሕገወጥ መንገድ የከተማዋን ሀብት ያለአግባብ ይዘው መቆየታቸውን ገልፀው ይህ ከዚህ በኋላ እንደማይቀጥል መረዳት ይገባል ብለዋል፡፡

ኅብረተሰቡ የሕዝብ ሀብት በስግብግብነት ሰብስበው በመያዝ ለግል ጥቅማቸው ያዋሉ ግለሰቦችን በማጋለጥ የከተማዋን ሀብት መጠበቅ ይኖርበታል ነው ያሉት፡፡

ምክትል ከንቲባዋ በአራዳ ክፍለ ከተማ የተጀመረው ሕገወጥ የቀበሌ ቤቶችን ለሕዝብ የማስተላለፍ ስራ በሁሉም ክፍለ ከተሞች ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

ለስራው መሳካት የኅብረተሰቡ ተሳትፎ ጉልህ እንደነበር ያወሱት ምክትል ከንቲባ አዳነች በቀጣይ በሚሰሩ ስራዎችም ተሳትፎውን አጠናክሮ እንዲቀጥልም አስገንዝበዋል፡፡

ቤቶቹ የተላለፉላቸው አቅመ ደካሞችና በችግር ላይ የነበሩ ወገኖች የዘመናት ጥያቄያቸው ስለተፈታላቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡

በወረዳ 6 ወጣት ማዕከል አካባቢ የዕድር እቃ ቤት ውስጥ ለአምስት ዓመታት መኖራቸውን የሚናገሩት ወይዘሮ መቅደስ አክሊሉ ችግራቸው ስለተፈታላቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል።

ከሶስት ልጆቻቸው ጋር ኩሽና ተከራይተው ይኖሩ እንደነበር የተናገሩት ወይዘሮ መቅደስ ፈንታው በበኩላቸው ያገኘሁት ቤት ብሞት እንኳን ልጆቼ ማረፊያ ስላገኙ ደስታዬ ወደር የለውም ብለዋል፡፡

የአራዳ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ሃና የሺንጉስ ከተማ አስተዳደሩ በጥናት የለያቸው 139 የቀበሌ መኖሪያ ቤቶች በችግር ውስጥ ለሚገኙና ለአቅመ ደካማ የኅብረተሰብ ክፍሎች መተላለፋቸውን ገልፀዋል፡፡

ለዚህ ስራ የከተማወ የጸጥታ ቢሮ፣ የክፍለ ከተማው ሴቶችና ወጣቶች አደረጃጀቶችና አመራሮች ያሳዩት ተሳትፎ ቀላል እንዳልነበረም አውስተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም