በሲዳማ ክልል ያለጭንብልና ያለጥንቃቄ የመደበኛ አገልግሎት ክልከላ ተግባራዊ ሊደረግ ነው

61

ሀዋሳ፣ ጥር 26/2013 (ኢዜአ) ሀዋሳን ጨምሮ በሲዳማ ክልል ሁሉም አካባቢዎች ኮሮናን ለመከላከል ያለጭንብል እና ያለጥንቃቄ መደበኛ አገልግሎት ክልከላ በአስገዳጅነት ተግባራዊ ሊደረግ መሆኑን የክልሉ ሠላምና ጸጥታ ቢሮ አስታወቀ።

በሌላ በኩል በደቡብ ክልል ትምህርት ቤቶች የኮሮና መከላከል ንቅናቄ ዘመቻ ነገ በይፋ እንደሚጀመር ተገልጿል።

የኮሮና ወረርሽኝ በመከላከል በኩል በማህበረሰቡ ዘንድ የተፈጠረውን መዘናጋት ለማስቀረት የሚያግዝ  ንቅናቄ ለመፍጠር በሀዋሳ ከተማ የውይይት መድረክ ሲካሄድ የሲዳማ ክልል ሠላምና ጸጥታ ቢሮ አቶ አለማየሁ ጢሞቲዮዎስ  እንዳሉት በተለይም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከተነሳ ወዲህ በማህበረሰቡ ዘንድ የተፈጠረው መዘናጋት የኮሮና ቫይረስ ስርጭት አሳሳቢ አድርጎታል።

በዚሁ  ከቀጠለ ሊከሰት የሚችለው ጉዳት አስከፊ መሆኑን ጠቅሰው ጉዳቱን አስቀድሞ ለማስቀረት የመከላከል ሥራዎችን በጠንካራ አቋምና ቅንጅት መምራትና መሥራት ይጠበቃል ብለዋል፡፡

በዚህ መነሻ ከዛሬ ጀምሮ ሀዋሳን ጨምሮ በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች የትኛውንም መደበኛ አገልግሎት ለማግኘት የአፍና አፍንጫ ጭምብል መልበስ፣ ያለመጨባበጥ ፣ ርቀትንና ንጽህናን መጠበቅን የመሳሰሉ የኮሮና መከላከል ጥንቃቄዎች ማድረግ በአስገዳጅ ሁኔታ ተግባራዊ እንደሚደረግ አስታውቀዋል፡፡

ከግለሰብ ጀምሮ ሁሉም ማህበራዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የተቀመጡ ክልከላዎችን ተላልፈው ሲገኙ የጸጥታ አካላት ሥርዓት በማሲያዝ እንዲያስፈጽሙ እንደሚደረግ ገልጸዋል።

የጸጥታ፣ትምህርት፣ጤና፣ መንገድና ትራንስፖርት ልማት ቢሮዎች በጋራ አፈጻጸሙን ክትትል እንዲያደርጉ መመሪያ መተላለፉን አቶ አለማየሁ ተናግረዋል፡፡ 

የክልሉ የህብረተሰብ ጤና ኢንስትቲዩትና የድንገተኛ አደጋዎች ማስተባበሪያ ማዕከል ሃላፊ ዶክተር ማቴ መንገሻ በበኩላቸው በእስካሁኑ ሂደት በክልሉ ምርመራ ከተደረገላቸው ከ52 ሺህ በላይ ዜጎች መካከል ከ3 ሺህ 950 በላይ በቫይረሱ እንደተያዙ መረጋገጡን አስታውሰዋል፡፡

ከእነዚህ የ67 ዜጎች ህይወት ሲልፍ 97 በቤት ለይቶ ማቆያ እንዲሁም ሶሰት በጠና ታመው ለመተንፈስ የማሽን ድጋፍ ላይ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በዚህ ቁጥር መሠረት ከተመረመሩ አንድ መቶ ሰዎች መካከል 12 ቫይረሱ ያለበት መሆኑን እንደሚጠቁም ገልጾ በክልሉ የቫይረሱ ስርጭት አሳሳቢ በሚባል ደረጃ ላይ መሆኑን ጦቁመዋል፡፡

ምልክት ሳይኖራቸው ቫይረሱ የሚገኝባቸው እየተበራከቱ መምጣቱ ስጋቱን ከፍተኛ እንደሚያደርገው አስረድተዋል፡፡


ዜጎችን ለመታደግ ያለጭንብል እና ሌሎች የኮሮና መከላከል ጥንቃቄ ሳያደርግ መደበኛ አገልግሎት ክልከላውን በአግባቡ መተግበር እንደሚገባ አመልክተው ግንዛቤ የመፍጠርና ለመመሪያዎች ተግባራዊነት የህግ ከለላ ለማጠናከር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትኩረት እየተሠራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የመከላከል አስገዳጅ ህጎችን በመፈጸም፣በማስፈጸምና ጠንካራ የቁጥጥር ሥራ በማከናወን የበኩላቸውን እንደሚወጡ የገለጹት ደግሞ የክልሉ ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ስዩም ጋሳ ናቸው።


ለአንድ ቀን በተካሄደው የንቅናቄ መድረኩ ከክልሉ ሁሉም መዋቅር የተወጣጡ የጤና፣ ሠላምና ጸጥታ አካላት ተሳትፈዋል፡፡


በሌላ በኩል በደቡብ ክልል ትምህርት ቤቶች የኮሮና መከላከል የንቅናቄ ዘመቻ ነገ በይፋ እንደሚጀመር የክልሉ ትምህርት ቢሮ ገልጿል።

ዘመቻውን አስመልክተው የቢሮው ኃላፊ አቶ ማሄ ቦዳ እንዳስታወቁት በኮሮና ምክንያት ተቋርጦ የነበረውን የመማር ማስተማር ሂደት ሲጀመር  መምህራን፣ ተማሪዎችንና ወላጆችን በማነቃነቅ ሰፊ የግንዛቤ ሥራ ተከናውናል።

ህብረተሰቡን በስፋት በማስተባበርም አዳዲስ የመማሪያ ክፍሎችን ከመገንባት ጀምሮ ለኮሮና መከላከል የሚያስፈልጉ ግብአቶች በትምህርት ቤቶች ላይ እንዲሟሉ መደረጉን አውስተዋል።

ሆኖም በአሁኑ ወቅት በሽታውን በመከላከሉ ረገድ በትምህርት ማህበረሰቡ ዘንድ በመቀዛቀዙ ይህንን ለማስተካከል የንቅናቄ ዘመቻ ከነገ ጀምሮ በክልሉ ስልጤ ዞን ወራቤ ከተማ በይፋ እንደሚጀመርም ገልጸዋል፡፡

በዘመቻው የተመረጡ ተማሪዎችና መምህራን በሁሉም የትምህርት ቤቶች 500 ሜትር ርቀት ዙሪያ የጎዳና ላይ የእግር ጉዞ በማድረግ ህብረተሰቡን ስለ ጭንብል አጠቃቀምና መወሰድ ስላለባቸው ጥንቃቄዎች ግንዛቤ ለማስጨበጥ እንደሚሰሩ አስታውቀዋል፡፡

የደቡብ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ አቅናው ካውዛ በበኩላቸው በኢትዮጵያ የፅኑ ህሙማን ቁጥር መጨመር ከፍተኛ ሥጋት መፍጠሩን ተናግረዋል ፡፡

በክልሉ አምስት ሚሊዮን የሚጠጉ ተማሪዎች በትምህርት ገበታ ላይ እንደሚገኙ ጠቅሰው ከፍተኛ ቁጥር ያለውን የትምህርት ማህበረሰብ መለወጥ ከቻልን ሌላውን ህብረተሰብ ለመለወጥ ምቹ ሁኔታ እንፈጥራለን ብለዋል ፡፡

በትምህርት ቤቶች ላይ ያለው የመከላከል ስራ መቀዛቀዝ እየተስተዋለበትም ቢሆንም ከውጪው ማህበረሰብ የተሻለ እንደሆነ የጠቆሙት አቶ አቅናው በየደረጃው ያለው የጤናው ሴክተርም አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም