የፋይናንስ አቅርቦትና አስተዳደር ችግር ለግብርና ዕድገት ማነቆ ሆኗል - ግብርና ሚኒስቴር

98

አዲስ አበባ፣ ጥር 26 /2013 (ኢዜአ)  የፋይናንስ አቅርቦትና አስተዳደር ችግር ለግብርና ዘርፍ ዕድገት ማነቆ መሆኑን ግብርና ሚኒስቴር ገለፀ።

ሚኒስቴሩ "የገጠር የፋይናንስ አቅርቦት ለግብርናው ዕድገት" በሚል ከባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቷል።

የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ዑመር ሁሴን ከግብርናው ዕድገት መሰናክሎች የፋይናንስ ተቋማት የብድር አቅርቦትና ከመንግስት የሚመደበው በጀት ማነስ ዋነኞቹ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ባንኮች ለማበደር ያስቀመጧቸው የመሬት ደረጃዎች የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘቡ በመሆናቸው በዘርፉ ለተሰማሩና መሰማራት ለሚፈልጉ ብድር ለማግኘት ማነቆ ሆኗል ብለዋል።

የወጡ ፖሊሲዎች በአግባቡ እንደማይተገበሩና ባንኮችም ለዘርፉ በበቂ ሁኔታ ብድር የማመቻቸት ችግሮች እንዳሉባቸው ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

ሚኒስትሩ የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ እያደገ የመጣውን የአገሪቷን የምርት ፍላጎት ለማሟላትና የተሻለ የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት አማራጭ የፋይናንስ ተቋማትና የተሻለ አስተዳደር ይፈልጋል ነው ያሉት።

ለዚህም እንደ አማራጭ የግብርና ባንኮችና ሌሎች አማራጭ የፋይናንስ ተቋማት ቢቋቋሙ ሲሉ ሚኒስትሩ ሃሳብ አቅርበዋል።

የተበዳሪውን ንቃተ ህሊና ለማዳበርና የሚሰጠውን የብድር አቅርቦት ዕድል እንዲጠቀም የግንዛቤ ስራ እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ አካታችነት ጽህፈት ቤት ከፍተኛ መኮንን አቶ ፍቅረማርቆስ አበበ በበኩላቸው የግብርናው ዘርፍ ለኢኮኖሚው እያበረከተ ካለው አስተዋጽኦ አንጻር በቂ የብድር አገልግሎት ተሰጥቷል ማለት አይቻልም ይላሉ።

እንደ እርሳቸው ገለፃ በአገሪቷ ለግብርናው ዘርፍ እየተሰጠ ያለው ከአጠቃላይ የብድር አገልግሎት ከ10 በመቶ አይበልጥም።

ችግሩን ለመፍታት ዘላቂና አስተማማኝ የፋይናንስ ስርዓት መዘርጋት ወሳኝ መሆኑንም አክለዋል።

በቅርቡም በዘርፉ ለተሰማሩ ባለሃብቶች ተንቀሳቃሽ ንብረቶችን በማስያዝ ብድር የሚያገኙበት አሰራር ተመቻችቷል ብለዋል።

በተጨማሪም ባንኮች በዓመት ከሚሰጡት ብድር አምስት በመቶ የሚሆነውን በግብርና ዘርፉ ለተሰማሩ ባለሃብቶች እንዲሰጡ መመሪያ ወጥቷል።

ባንኩ እነዚህና ሌሎች ዘርፉን የሚያበረታቱ ሕጎችና መመሪያዎች መተግበራቸውን በአጽንኦት ይከታተላል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት ዶክተር ዮሐንስ አያሌው በበኩላቸው ባንኩ የተቋቋመው በዋነኝነት በግብርናና በኢንዱስትሪ ዘርፎች ለተሰማሩ የብድር አገልግሎት ለመስጠት ቢሆንም በዚህ ለመጠቀም የሚመጡት ጥቂቶች ናቸው ይላሉ።

ለዚህም በመንግስት የተፈቀደውን ብድር ለመጠቀም የተቀመጡ ገደቦች የአገሪቷን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘቡ መሆን፣ የወለድ ተመን ማነስና የማበረታቻ አለመኖር ተግዳሮቶች ናቸው ብለዋል።

የውይይት መድረኩ ዓላማም በግብርናው ዘርፍ ያሉ የፋይናንስ አቅርቦት ችግሮችን በጋራ በመፍታት ዘርፉ ለኢኮኖሚው እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦ ማሳደግ እንደሆነ ጠቁመዋል።

በዘርፉ ለመሰማራት ፍላጎት ያላቸው ዜጎች ያሉትን አማራጮች በመጠቀም ወደስራ እንዲሰማሩ ማድረግም እንዲሁ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም