በሰቃ ጨቆርሰ ወረዳ የተሽከርካሪ አደጋ የሰባት ሰዎችን ህይወት አጠፋ

110
ጅማ ሀምሌ 18/2010 ጅማ ዞን ሰቃ ጨቆርሰ ወረዳ ዛሬ በደረሰ የተሽከርካሪ አደጋ   የሰባት ሰዎች ህይወት ማለፉን ፖሊስ አስታወቀ። አደጋው የደረሰው ረፋድ አራት ሰዓት አካባቢ የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3-7320 ኢት የሆነ የህዝብ ማመላለሻ አውቶቡስ ከሚዛን ወደ አዲሰ አበባ በመጓዝ ላይ እንዳለ በሌላኛው አቅጣጫ ከሰቃ ወደ ሸቤ ከተማ በመጓዝ ላይ ከነበረ  የሰለዳ ቁጥሩ ኮድ 3- 40107 ኦሮ ከሆነ ዶልፊን አነስተኛ የህዝብ ማመላለሻ ጋር በመጋጨቱ ነው። በዞኑ ፖሊስ ጽህፈት ቤት የትራፊክ ዲቨዚዮን ኃላፊ ምክትል ኮማንደር ሰለሞን አየለ እንዳስታወቁት በአደጋው ህይወታቸው ካለፈው ሌላ  በ22 ሰዎች ላይ ከባድ እና  ቀላል የአካል ጉዳት ደርሷል፡፡ ከማቾቹ ውስጥ ሾፌሩን ጨምሮ ስድስቱ  በዶልፊኑ ቀሪው አንድ  ሰው ደግሞ  በአውቶቡስ ተሳፍረው ከነበሩት ውስጥ ናቸው። በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች  በሰቃ እና ጅማ ሆስፒታሎች  የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው መሆኑን ምክትል ኮማንደር ሰለሞን ተናግረዋል፡፡ የሟቾቹ አስክሬን ቤተሰቦቻቸው እስኪረከቡ  በጅማ ሪፈራል ሆስፒታል እንዲቆይ መደረጉን ጠቅሰው የአውቶቡሱ ሹፌር ተይዞ የአደጋውን መንስኤ በማጣራት ላይ መሆኑንም አመልክተዋል። የሰቃ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ሁሴን መሃመድ በአደጋው ከባድ ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ወደ ጅማ ሪፈራል ሆስፒታል መላካቸውን ጠቅሰው ቀላል ጉዳት የደረሰባቸው ደሞ በሆስፒታሉ ህክምና እየተደረገላቸው እንደሚገኙ ገልጸዋል። የአካባቢው ህብረተሰብ ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ፈጥኖ ወደ  ህክምና ተቋም ለማምጣት ያሳየውን ትብብር አድንቀውል፡፡ ሜዲካል ዳይሬክተሩ በደረሰው አደጋ የተሰማቸውን ሀዘን ገልጸው ለሟቾቹ  ቤተሰቦች መጽናናትን ተመኝተዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም