በአፍሪካ አካታችና ጥራት ያለው ትምህርት ለማዳረስ እንደሚሰሩ እጩ ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማሪያም ተናገሩ

113

አዲስ አበባ ጥር 26/2013 (ኢዜአ) በአፍሪካ አካታችና ጥራት ያለው ትምህርት ለማዳረስ እንደሚሰሩ የአፍሪካ ህብረት የትምህርት፣ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ፈጠራ እጩ ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም ተናገሩ ።

የፕሮፈሰር ሂሩት ለአፍሪካ ህብረት የትምህርት፣ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ፈጠራ ኮሚሽነርነት የምረጡኝ ዘመቻ መርሃግብር ትላንት ተካሄዷል።

ኢትዮጵያ ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያምን ለህብረቱ ኮሚሽነርነት በዕጩነት አቅርባለች።

የኮሚሽኑ ዕጩ ሆነው የቀረቡት ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም ያላቸውን ልምድ፣ የትምህርት ዝግጅትና ያለፉባቸውን ሃላፊነቶች አካፍለዋል።

በአፍሪካ በትምህርት፣ ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ፈጠራ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን በመዘርዘር ሊሰሯቸው ያቀዷቸውን አቅርበዋል።

ዓለም የተለያዩ የአብዮት ደረጃዎችን በማለፍ በአሁኑ ወቅት የቴክኖሎጂ አብዮት ላይ እንደምትገኝ በማስረዳት አፍሪካም እኩል መሄድ እንዳለባት በአጽእኖት አንስተዋል።

ለዚህም የትምህርት፣ ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ፈጠራ ያላቸውን ፋይዳ በመዘርዘር በአፍሪካውያን ወጣቶች ላይ ትኩረት በማድረግ እንደሚሰሩ አብራርተዋል።

በአፍሪከ አካታች ጥራት ያለው ትምህርት እውን በማድረግ የአህጉሩን እምቅ የወጣት ሃብት መጠቀም ላይ የመስራት እቅድ እንዳላቸው ገልጸዋል።

በህብረቱ ኮሚሽነርነት ቢመረጡ በትምህርት ጥራትና በሳይንስና ቴክኖሎጂ ለአፍሪካ የበኩላቸውን እንደሚያደርጉ ቃል ገብተው ድጋፍ እንዲደረግላቸውም ጠይቀዋል።

በመርሃግብሩ ላይ የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የአፍሪካ ህብረት የትምህርት፣ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ፈጠራ ኮሚሽን የአህጉሪቱ ነጻ የንግድ ቀጣና ትግበራን በቴክኖሎጂ በማገዝ በኩል ያለውን ቁልፍ ሚና አንስተዋል።

ኢትዮጵያም ይህን ዕድል በመጠቀምና አህጉሩን ለማገልገል በትምህርት ዝግጁነት፣ በአመራር ችሎታና በስራ ልምድ የካበተ ልምድ ያላቸውን ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያምን ለዕጩነት አቅርባለች ነው ያሉት።

አዳዲስ የፈጠራ ውጤቶችና የቴክኖሎጂ ግብአቶች በመጠቀም የአፍሪካን ምጣኔ ሃብት በማዘመን በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ማድረግ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።

ፕሮፌሰር ሂሩት በተመራማሪነት፣ በመሪነትና በሌሎችም ያለፉባቸውና አሁን እያገለገሉባቸው የሚገኙ የሃላፊነት ቦታዎችን አቶ ደመቀ ዘርዝረዋል።

በአመራር ጥበባቸው ለህብረቱ የትምህርት፣ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ፈጠራ ኮሚሽን እሴት እንደሚጨምሩ እምነታቸውን ገልጸው ዲፕሎማቶች፣ አምባሳደሮችና ሌሎች በመድረኩ የተገኙ አካላት ድጋፍ እንዲያደረጉም አቶ ደመቀ ጠይቀዋል።

በመርሃ ግብሩ ሚኒስትሮች፣ ዲፕሎማቶች፣ ታዋቂ ሰዎችና ሌሎችም የክብር እንግዶች የተገኙ ሲሆን የሚያውቋቸውም ፕሮፌሰር ሂሩት ስላላቸው ልምድና ብቃት ምስክርነት ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም