በትግራይ ደቡባዊ ዞን 70 ሺህ ወጣቶች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሰማርተዋል

53
ማይጨው ሀምሌ 18/2010 በትግራይ ደቡባዊ ዞን 70 ሺህ ያህል ወጣቶች በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መሰማራታቸውን የዞኑ ወጣቶች ማህበር አስታወቀ። የማህበሩ ሊቀመንበር ወጣት የማነ ክፍለማርያም ዛሬ እንዳስታወቀው ወጣቶቹ በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተሰማሩት በዞኑ ማይጨው፣ ኮረምና አላማጣ ከተሞችን ጨምሮ በ93 የገጠር ቀበሌዎች ነው፡፡ በተለያዩ የልማት ስራዎች ከተሰማሩ ወጣቶች መካከል 60 በመቶ ያህሉ የ10ኛና የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና የወሰዱ ናቸው፡፡ ቀሪዎቹ  ከዩኒቨርሰቲዎች የዘንድሮ ተመራቂዎችና ተማሪዎች መሆናቸውን ገልጿል፡፡ ወጣቶቹ የችግኝ ተከላን ጨምሮ የአርሶአደሩን ማሳ የጎርፍ መውረጃ ቦዮች ጠረጋ፣ ዘር የመዝራት፣ አረም የማስወገድና ተጓዳኝ የልማት ስራዎችን በማከናወን ድጋፍ እያደረጉ ነው። በተጨማሪም በአካባቢው ለሚገኙ ጎልማሶችና የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች የማጠናከርያ ትምህርት በመስጠት ላይ እንደሚገኙም  አስታውቋል፡፡ በከተሞች አካባቢም የጎርፍ መቀልበሻ ቦዮች ጠረጋ ስራ በማካሄድ ነዋሪዎችን ከጎርድ አደጋ የመጠበቅ ተግባር በማከናወን ላይ እንደሚገኙም አመልክቷል። ከዩኒቨርሰቲ ተመርቀው የወጡ ወጣቶችም  በተለያዩ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ተመድበው አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆናቸውን ገልጿል፡፡ የእንዳመሆኒ ወረዳ ነዋሪና ወጣት ስዩም አብርሃ  በሰጠው አስተያየት የእረፍት ጊዜውን በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በማሳለፍ ላይ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ከጓዶኞቹ ጋር በመሆን በችግኝ ተከላ በመሳተፍ ላይ መሆኑን ገልጿል፡፡ በቅርቡ ከመቀሌ ዩኒቨርስቲ የተመረቀው ላሌው የወረዳ ነዋሪ ወጣት ብርሃኑ ሓጎስ በበኩሉ፣  ከጓደኞቹ ጋር በመሆን ለአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠት ላይ መሆኑን አስታውቋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም