ኢትዮጵያና እስራኤል በመረጃና ደህንነት ዘርፍ የጀመሩትን ሁሉን አቀፍ ትብብር አጠናክረው ይቀጥላሉ -አምባሳደር ራፋኤል ሞራቭ

131

ጥር 25/2013(ኢዜአ)በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር ራፋኤል ሞራቭ ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ተመሰገን ጥሩነህ ጋር በዛሬው ዕለት ውይይት አድርገዋል።

የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎትና የእስራኤል የመረጃና ደህንነት ተቋም ሞሳድ የጀመሩት ሁሉን አቀፍ የትብብርና የአጋርነት ግንኙነት ይበልጥ ተጠናክሮ ስለሚቀጥልባቸው ጉዳዮች መወያየታቸውን አገልግሎት መስሪያ ቤቱ ለመገናኛ ብዙሃን በላከው መረጃ አመልክቷል፡፡

የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ተመስገን ጥሩነህ ተቋማቸው ከእስራኤሉ አቻ የመረጀና ደህንነት ተቋም ጋር በመረጃ ልውውጥ፤ ሽብርተኝነትን በጋር በመከላከል እንዲሁም በአቅም ግንባታና በቴክኖሎጂ ዘርፎች የጀመረው የትብብር ማዕቀፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በውይይቱ ወቅት ለተሰናባቹ አምባሳደር ራፋኤል ሞራቭ ገልጸዉላቸዋል፡፡

የአገልግሎት ጊዜያቸውን ያጠናቀቁት አምባሳደር ራፋኤል ሞራቭ እስራኤል በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት ላይ ወሳኝ ሚና ካላት ኢትዮጵያ ጋር በመረጃና ደህንነት ዘርፍ ተባብራ የመሥራት ከፍተኛ ፍላጎቷን በቆይታቸው ወቅት ማሳካታችውን ገልፀዋል::

በቀጣይ በኢትዮጵያ እስራኤል ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር በመሆን ለሚሾሙትም ይህን ተመሳሳይ የትብብር ተልዕኮ እንዲያስቀጥሉ መልዕክታቸውን እንደሚያስተላልፉም ገልጸዋል።

የእስራኤል የደህንነት ምክትል ሚኒስትር ጋዲ ይቫርካን እንዲሁም በኢትዮጵያና በአፍሪካ የሞሳድ ቢሮ ኃላፊ ኢትዮጵያና እስራኤል በመረጃና ደህንነት ዘርፉ ያላቸውን ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር የሚያስችላቸውን ስምምነት በ2013 ዓ.ም መፈጸማቸውም አገልግሎት መስሪያ ቤቱ በላከው መረጃ አስታውሷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም