የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ከተ.መ.ድ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልእክተኛ ጋር ተወያዩ

154

አዲስ አበባ፤ ጥር 25 ቀን 2013(ኢዜአ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልእክተኛ ፓርፋት ኦናንጋ አንያኛ((Parfait Onanga Anyanga)ን ትላንት በቢሮአቸው አነጋግረዋል።

ውይይቱ የተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ፊሊፖ ግራንዲ በትግራይ ክልል በሁለት ካምፕ የኤርትራ ስደተኞች ያሉበትን ሁኔታ ለመገንዘብ ያደረጉት ጉብኝት፣ የትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ፣ በክልሉ የሰብአዊ እርዳታ ለማድረስ እየተደረገው ያለው ርብርብ ፣ የመልሶ ማቋቋም ሥራ ፣ የህወሃት ጁንታ ያፈራረሳቸው መሰረተ ልማቶች መልሶ ግንባታ ላይ ያተኮረ እንደነበር ተገልጿል።

በተጨማሪም የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር እያደረገ ያለው ጥረትና ያለበት ውስንነት፣ የ6ኛው ብሄራዊ ምርጫ ዝግጅት ላይ እንዳለ ነገር ግን በትግራይ ክልል ምርጫ ለማካሄድ ያለው ሁኔታ የማይፈቅድ መሆኑን፣ በኢትዮ-ሱዳን የድንበር ጉዳይና የኢትዮጵያ መንግስት አቋም ጉዳዩ በድርድርና በውይይት ብቻ እንደሚፈታ እምነት እንዳለው አምባሳደር ሬድዋን በዝርዝር ገልፀውላቸዋል።

በትግራይ ክልል የሰብአዊ እርዳታ በሁሉ ቦታ ተደራሽ ለማድረግ መንግስት በመስራት ላይ እንዳለ፣ የጁንታ አባላትና አጋፋሪዎቹ መንግስት በክልሉ እያደረገ ያለው የሰብአዊ እርዳታ አሳንሰው የማቅረብና ጉዳዩን ሚዛናዊ ባልሆነ መንገድ በማቅረብ ላይ እንደሚገኙ፣ በለጋሽ ድርጅቶችና በሌሎች የሚነሱ ሃሳቦችና ጥያቄዎች ዙሪያ ተወያይተዋል።

አምባሳደር ሬድዋን በትግራይ ክልል የተደረገው የህግ የበላይነትን የማስከበር ዘመቻ የህወሃት ጁንታ ቡድን በአገር መከላከያ ሰራዊት የሰሜን እዝ አባላት ላይ በተኙበት ጥቃት በመፈፀሙ ምክንያት ተገዶ የተገባበት የአገር ህልውና እና ሉዓላዊነትን ለመታደግ የተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።

የህወሃት ቡድን በክልሉ በሰፊው ሲያደርግ የነበረው የጦርነት የፖሊቲካ ፕሮፓጋንዳ በሶስት ሳምንታት ጊዜ በተደረገ ዘመቻ መንግስት ክልሉን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር መቻሉ፣ የህግ ማስከበሩን ሥራ ቀጠናዊ ችግር ለማስመሰል የጎረቤት አገር ኤርትራ ወታደሮች ትግራይ ውስጥ ገብተው በኦፕሬሽኑ ላይ ተሳትፈዋል የሚል የውንጀላ ክስ ሲያቀርቡ መቆየታቸውንም ገልጸዋል።

መንግስት በትግራይ ክልል የህወሃት ጁንታ ያወደመው መሰረተ ልማት፣ በክልሉ ያሉ በርካታ ቁጥር ያላቸው ፍርደኞችን ፈትቶ በመልቀቅ ንብረት ዘረፋና ማህበራዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ ያደረሰውን ውድመት መልሶ ለመገንባት ሶስት ክላስተር መቋቋሙንም ነው የጠቀሱት።

በዚህም የጤና፣የትምህርት እና ትራንስፖርት አገልግሎቶች ወደ ነበሩበት እና የህዝቡን ኑሮ ወደ መደበኛ ለመመለስ የሚያስችል ሥራ ሶስቱም ሚንስቴር መ/ቤቶች አስፈላጊውን ርብርብ በማድረግ ላይ እንዳሉ ሚኒስትር ዴኤታው ጨምረው ገልፀውላቸዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልእክተኛ ፓርፋት ኦናንጋ አንያኛ((Parfait Onanga Anyanga) በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንግስት ለተባበሩት መንግስታት ልዑካን ቡድን ለሥራ ወደ አዲስ አበባ በሚመጡበት ጊዜ ለተደረገላቸው መልካም አቀባበል ምስጋና አቅርበዋል።

ሰብአዊ እርዳታን በትግራይ ክልል ተደራሽ ለማድረግ መንግስት እያደረገው ያለው ጥረት እንደሚያደንቁ በመጥቀስ፤ የኢትዮጵያ መንግስት በሽግግር ላይ በመሆኑ መንግስታት በሽግግር የሚያልፋበት ያለመረጋጋትና የደህንነት ስጋት ሊያጋጥም እንደሚችል የሚጠበቅ መሆኑን እንደሚረዱም ገልፀዋል።

የሰብአዊ ድጋፍን በማድረስ የኢትዮጵያ መንግሥትን በማገዝ ሊፈጠር የሚችልን ችግር ማስቀረት እንደሚቻልም ነው የተናገሩት።

ልዩ መልዕክተኛው በኢትዮጵያና በሱዳን ያለው የድንበር ጉዳይ የኢትዮጵያ መንግስት ጉዳዩን በሰላማዊ መንገድ ለመፈታት የያዘው አቋም ትክክል መሆኑን በመጠቆም፤ ትኩረት ያሻቸዋል ያሏቸው ጉዳዮች ላይ አስተያየትና ጥያቄ አቅርበዋል።

አምባሳደር ሬድዋን ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽ በመስጠት በትግራይ ክልል የሚደረግ ሁሉን አቀፍ ርብርብ የበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥል መንግስት ይሠራል ብለዋል።

በሀገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ የተሻለ ግንዛቤ ማግኘታቸውን ልዩ መልክተኛው በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ መግለጻቸውን ከውጭ ሚኒስቴር ጉዳይ ቃል አቀባይ ፅ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም