የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶቹ ለወጣቶች የስራ ዕድል አስገኝተዋል

78

አዲስ አበባ፣ ጥር 25 /2013 (ኢዜአ)የአጅማ ጫጫና የካሊድ ዲጆ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች የስራ ዕድል እንዳስገኙላቸው የአካባቢዎቹ ወጣቶች ገለጹ።

በግንባታ ላይ የሚገኙት የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶቹ እስካሁን ከ700 በላይ ለሆኑ ወጣቶች የስራ ዕድል ፈጥረዋል።

የስራ ዕድል ተጠቃሚዎቹ ወጣቶች ለኢዜአ እንደገለጹት በፕሮጀክቶቹ መጀመር የተሻለ ሕይወት መምራት እንደሚችሉ ተስፋ ሰንቀዋል።

ክቴ ገበየሁ በአጅማ ጫጫ መስኖ ልማት ፕሮጀክት በሠዓት ተቆጣጣሪነት በመስራት ላይ ትገኛለች።

የ10ኛ ክፍል ፈተና ወስዳ በውጤቷ በመሰናዶ ትምህርት መቀጠል ባለመቻሏ ስራ ብታፈላልግም በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ ስራ በመቀዛቀዙ ሳታገኝ መቆየቷን ገልፃለች።

የቤተሰቦቹን መሬት በማረስ ይተዳደር የነበረው ወጣት የሺጥላ ንጋትም ፕሮጀክቱ በአካባቢው በመጀመሩ ከግብርና ስራው ጎን ለጎን በጥበቃ ሠራተኝነት መቀጠሩንና ተጨማሪ ስራ ማግኘቱን ተናግሯል።

ወጣት ሰለሞን መርሻ እና ንጉሴ ጌታቸውም ፕሮጀክቱ ሙያ ለመልመድና ገንዘብ ለመቆጠብ እንዳስቻላቸው ተናግረዋል።

ቀደም ሲል ከመኖሪያ አካባቢው ርቆ ይሰራ እንደነበርና የካሊድ ዲጆ ፕሮጀክት መጀመር በአካባቢው እንዲሰራ እንዳደረገው የገለጸው ደግሞ የግንባታው ረዳት ተቆጣጣሪ ሀብታሙ ሁሴን ነው።

በተመሳሳይ በፕሮጀክቱ በሠዓት ቶጣጣሪነት እየሰሩ የሚገኙት ራቢያ ሳጅንና ሳዲቅ ፋሪስ ፕሮጀክቱ በአካባቢያቸው የስራ እዕድል እንዳስገኘላቸው ገልፀዋል።

የመስኖ ልማት ኮሚሽነር ዶክተር ኢንጂነር ወንድሙ ተክሌ ግንባታቸው በቅርቡ በተጀመረው በላይኛው ጉደር፣ በአጅማ ጫጫና በካሊድ ዲጆ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች በርካቶች የስራ ዕድል አግኝተዋል ይላሉ።

ፕሮጀክቶቹ በቀጣይም ከ5 ሺህ በላይ የቀን ሠራተኞች የስራ ዕድል እንዲያገኙ ያስችላሉ ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም