የቡሬ የተቀናጀ የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ የመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ ተጠናቆ ለአገልግሎት ተዘጋጀ

61

ባህርዳር፤ ጥር 25/2013(ኢዜአ) የቡሬ የተቀናጀ የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ የመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ አራት ቢሊዮን 600 ሚሊዮን ብር በሆነ ወጪ በማጠናቀቅ ለአገልግሎት መዘጋጀቱን የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አስታወቀ።

ፓርኩ በመጪው እሁድ የፌደራልና ክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት ይመረቃል።

የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ደሴ አሰሜ ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት የኢንዱስትሪ ፓርኩ የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ የተጀመረው በ2010 ዓ.ም. በጀት ዓመት ነው።

በክልሉ በሚገኙ የልማት ድርጅቶች ተቋራጭነት የተጀመረው የመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ በአንድ ዓመት ተኩል ግንባታውን አጠናቆ ወደ ማምረት ስራ ለማስገባት ታስቦ እንደነበር አስረድተዋል።

በተቋራጮች ልምድና አቅም ማነስ፣ በግንባታ ቁሳቁስ አቅርቦት እጥረት፣ በዲዛይንና ሌሎች ተያያዥ ችግሮች ምክንያቶች ግንባታው ከተቀመጠለት ጊዜ ሊዘገይ እንደቻለም ጠቅሰዋል።

ፓርኩ የተገነባው የግብርና ምርቶች በስፋት በሚመረቱበት አካባቢ በመሆኑ ወደ ኢንዱስትሪው የሚገቡ አልሚ ባለሃብቶችንና የአካባቢውን አርሶ አደሮች ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው ብለዋል።

ይህም ግብርናውን አዘምኖና ከኢንዱስትሪው ጋር አስተሳስሮ የግብርና ምርትን በማቀነባበር የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኝ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢንዱስትሪ ፓርኩ አጠቃላይ በአንድ ሺህ ሄክታር እንደሚገነባ አመልክተው የመጀመሪያው ምዕራፍ ተገንብቶ የተጠናቀቀው በ260 ሄክታር መሬት እንደሆነም ተናግረዋል።

ፓርኩ በውስጡ የገበያ ማዕከል፣ የአንድ ማዕከል አገልግሎት፣ የአስተዳደር ህንፃ፣ ትምህርት ቤት፣ ክሊኒክ፣ የህፃናት ማቆያ፣ የእሳት አደጋ መከላከያ፣ የውሃ ጉድጓድና ማጠራቀሚያ እና 13 ኪሎ ሜትር የአስፓልት መንገድን በማካተት የተገነባ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህም ባለሀብቶች ድካምና ወጭ በመቀነስ ሙሉ አገልግሎታቸውን በፓርኩ ውስጥ እንዲያገኙ እንደሚያስችል አስረድተዋል።

የመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ በተጠናቀቀው ፓርኩ አልሚዎች ወደማምረት ስራ ሲገቡ ለ25 ሺህ ዜጎች ቋሚ የስራ እዕድል እንደሚፈጥር የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ ተናግረዋል።

የኢንዱስትሪ ፓርኩ የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማስፋፋትና ግብርናን ለማዘመን እንዲሰራ የተገነባ በመሆኑ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለውም አስታውቀዋል።

እስካሁንም በፓርኩ ውስጥ ሶሰት ባለሃብቶች ገብተው ዘጠኝ የተለያዩ ኢንዱስትሪዎችን በራሳቸው ዲዛይን እየገነቡ መሆኑን ጠቁመው ከእነዚህም የሰባቱ ባለቤት " ሪች ላንድ " የተባለ ካምፓኒ መሆኑን ገልጸዋል።

ከሰባቱ ውስጥም ሁለቱ የ"ፕሮቲን ፓውደር " ማምረቻና የዘይት ፋብሪካዎች ግንባታቸው ተጠናቆ ማምረት መጀመራቸው ተጠቅሷል።

በለማው ፓርክ ውስጥ ለማምረቻ ብቻ የተዘጋጀ 142 ሄክታር መሬት ያለ በመሆኑ ባለሃብቶች ገብተው ቢያለሙ ራሳቸውንና ሀገራቸውን ተጠቃሚ እንደሚያደርጉ አቶ ደሴ አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም