በመተከል ተከስቶ የነበረው የጸጥታ ችግር ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ስጋት አይሆንም … የመተከል የተቀናጀ ግብረ ሃይል

1542

መተከል፤ ጥር 23/2013(ኢዜአ) በመተከል ተከስቶ የነበረው የጸጥታ ችግር ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ስጋት እንደማይሆን የዞኑ የተቀናጀ ግብረ -ሃይል አስታወቀ።

ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን በማንኛውም ጊዜ ማድረስ የሚያስችል አስተማማኝ የጸጥታ አደረጃጀት እንዳለም አረጋግጧል።

በመተከል ቡለንና ድባጤ ወረዳዎች የሽፍታው ቡድን አባላት በንጹሃን ላይ ባደረሱት ግድያና መፈናቀል በዞኑ የጸጥታ ስጋት ተፈጥሮ እንደነበረ ይታወሳል።

የጸጥታ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታትና ዞኑን ወደነበረበት ሰላም ለመመለስ በፌዴራል መንግስት የተዋቀረው ግብረ-ሃይል የጸጥታና ህግ ማስከበር ስራውን እንዲረከብ ተደርጓል።

በዚህም ግጭት የተከሰተባቸውን ጨምሮ ግጭት ሊከሰትባቸው ይችላል በተባሉ ቦታዎች አንፃራዊ ሰላም መስፈን ችሏል ነው የተባለው።

ግብረ-ሃይሉም የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ ሌሎች የዞኑ ወረዳዎችን በመመልከት ከግድቡ ሰራተኞችና ከህብረተሰቡ ጋር ውይይት አድርጓል።

የመተከልን የተቀናጀ ግብረ ሃይል የሚመሩት ሌተናል ጄኔራል አስራት ዴኔሮ እና ሌሎች የግብረ ሃይሉ አባላት ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጎብኝተዋል።

ሌተናል ጄኔራል አስራት ዴኔሮ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የግድቡ ግንባታ ሲጀመር ጀምሮ ጸጥታውን ታሳቢ ያደረገ የመከላከያና የፌደራል ፖሊስ አባላት አደረጃጀት ተፈጥሯል።

በመሆኑም በውስጥም ሆነ በድንበር ያሉ ጉዳዮች በትኩረት ክትትል እየተደረገባቸው በመሆኑ ስጋት አይኖርም ብለዋል።

የአገር መከላከያ ሰራዊት ከግድቡ ሰራተኞችና አመራሮች ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን የገለጹት ሌተናል ጄኔራል አስራት ዴኔሮ፤ ሃላፊነት በጎደላቸው ማህበራዊ ድረ- ገፆች የሚተላለፉት የተሳሳቱ መረጃዎች የመተከልን ነባራዊ ሁኔታ አይገልጹም ብለዋል።

ከዚህም ባሻገር ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚውል ግብዓት በማንኛውም ሰዓት ለመቅረብ የጸጥታ ስጋት የሌለበት የትራንስፖርት አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑንም አስታውቀዋል።

የጸጥታ ስጋት አለብን የሚሉ ተሽከርካሪዎችን ማጀብ ደግሞ የአገር መከላከያ ሰራዊቱ የተለመደ ስራው መሆኑንም ነው የጠቆሙት።