ከጣና ኃይቅ እምቦጭን በማስወገድ ለተሳተፉ አካላት የእውቅና አሰጣጥ መርሃግብር እየተካሄደ ነው

1563

ባህርዳር ጥር 23/2013 (ኢዜአ) በጣና ኃይቅ የተከሰተውን የእሞቦጭ አረም ለማስወገድ በተካሔደው ዘመቻ ለተሳተፉ አካላትና ተቋማት የእውቅና መስጠት ፕሮግራም በጎንደር ዙሪያ ወረዳ ለምባ ቀበሌ በመካሔድ ላይ ነው ።

የጣና ኃይቅና ሌሎች የውሃ አካላት ጥበቃና ልማት ኤጀንሲ ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ዘላለም ልየው ለኢዜአ እንዳሉት ፕሮግራሙ አረሙን በማስወገድ የተሳተፉ አካላትን ለማመስገን የተዘጋጀ ነው።

“ከጥቅምት 9 እስከ ታህሳስ 30 ለ66 ቀናት በተካሔደው ዘመቻ ግለሰቦች ፣ተቋማት፣ ባለሃብቶችና አርሶ አደሩ ርብርብ አድርገዋል” ብለዋል።

በተደረገው ዘመቻ በሃይቁ ውስጥና ዳርቻ ከተወረረው 4ሺህ 300 ሔክታር ውስጥ 94 በመቶ የሚሆነውን ማስወገድ መቻሉን ተናግረዋል።

በዚህ የእምቦጭ ማስወገድ ዘመቻ ስራ 3 መቶ 96ሺህ አርሶ አደሮች የተሳተፉ ሲሆን ለጉልበት ክፍያና ሌሎች ወጪዎች 75 ሚሊዮን ብር ወጪ መደረጉን አስታውሰዋል።

ዘመቻው አረሙን ማስወገድ እንደሚቻል ትልቅ ትምህርት ተወስዶበታል”ያሉት አቶ ዘላለም ቀሪውን አረም የማስወገድ፣ የታረመውን አረም የማቃጠልና አካባቢውን መልሶ የማልማት ትልቅ ስራ እንደሚጠይቅም ተናግረዋል።

ለዚህም ሁሉም የበኩሉን ርብርብ እንዲያደርግ ምክትል ስራ አስኪያጁ ጠይቀዋል።

በምስጋናና እውቅና ፕሮግራሙ የውሃ መስኖና ኤነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለና የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ፋንታ ማንደፍሮን ጨምሮ ሌሎችም ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በፕሮግራሙ በእምቦጭ አረም መከላከል ዘመቻ አበርክቷአቸው የላቀ ለሆነ ግለሰቦች፣ አርሶ አደሮች፣ ተቋማት፣ ባለሃብቶችና ለሌሎች አካላት እውቅና ይሰጣል ተብሏል።