ወጥነትና ግልፅነት የጎደለው አሰራር የሴቶችን የፖለቲካዊ ተሳትፎ እንዳሳነሰው ተገለጸ

73

ባህር ዳር፤ ጥር 22/2013 (ኢዜአ) ወጥነትና ግልፅነት የጎደለው አሰራር የሴቶችን የፖለቲካና ውሳኔ ሰጭነት ተሳትፎ አነስተኛ እንዲሆን አድርጎታል ሲሉ የአማራ ክልል ሴቶች፣ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ አስናቁ ድረስ ገለጹ።

የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎና የውሳኔ ሰጪነት ሚና ማሳገድ በሚቻልበት ዙሪያ የተዘጋጀ የምክክር መድረክ በባህር ዳር ከተማ ተካሄዷል።

የቢሮ ሃላፊዋ በመድረኩ እንዳሉት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎና የውሳኔ ሰጪነትን ክፍተት ለመሙላት በመንግስትና ድርጅት እየተሰራ ይገኛል።

በተጀመሩ ስራዎች ውጤቶች የተመዘገቡ ቢሆንም አሁንም የሴቶች ተሳትፎ ከፍተኛ ክፍተት እንደሚስተዋልበት ተናግረዋል።

እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ክልል ከህዝቡ ቁጥር ከግማሽ በላይ የያዙ፣ በትውልድ ቀረጻና የማህበረሰብ ግንባታ ላይ  ከፍተኛውን ድርሻ የሚጫወቱት ሴቶች ናቸው ብለዋል።

ሆኖም  ይህንን  ፋይዳ ግምት ውስጥ በማስገባት በሁሉም ዘርፍ ሴቶችን በማሳተፍ ተጠቃሚ በማድረግ በኩል ሰፊ ክፍተት እንዳለ ገልጸዋል።

"በፖለቲካና በውሳኔ ሰጪነት ቦታዎች ላይ የክልላችን ሴቶች ተሳትፎ ከ19 በመቶ ያልበለጠ ነው" ብለዋል።

ለዚህም ወጥነት ያለው ሴቶች የሚሳተፉበት ግልጽ የአሰራር ስርዓት አለመኖር፣ የአመለካከት ችግር ፣ የእርስ በእርስ አለመረዳዳትና የአመራር ቁርጠኝነት አለመኖር ተጠቃሾች መሆናቸውን አስረድተዋል።

ችግሩን ለመፍታትም ከሴቶችና ወጣት አደረጃጀቶች ፣ዩኒቨርሲቲዎችና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር በመሆን የአጭርና የረጅም ጊዜ የአቅም ማጎልበቻ ስልጠናዎችን የመስጠት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

የሴቶች ፖለቲካዊ ተሳትፎና ውሳኔ ሰጪነት ተሳትፎ ኢ-ፍታዊነት ተፈጥሮዊ ሳይሆን ማህበረሰብአዊ ስሪት ነው ያሉት ደግሞ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ፈንታ ማንደፍሮ ናቸው።

ብዙ ጊዜ ወንድ ፖለቲከኞች  ሴት  ፖለቲከኞችን በራሳቸው ጥላ ሥር እንዲሆኑ እንጅ እራሳቸውን ችለው እንዲቆሙ የማድረግ ችግር እንዳለ ተናግረዋል።

ሴቶች እራሳቸውን ችለው በፖለቲካ መድረክ እንዲቆሙ ካልተደረገ የማህበረሰብ ተገቢ ድምጽ መሆን እንደማይችሉ አስረድተዋል።

"ሴት ፖለቲከኞችንና አመራሮችን በቁጥር እናብዛ ሳይሆን እሳቤያችን እናስተካክል፤ አሳቤያችንን ካስተካከልን በምንሰራው ስራ ሁሉ ሴቶችን መፈለግ እንጀምራለን " ብለዋል።

ለአንድ ቀን በተካሄደው የምክክር መድረኩ የክልሉ መስተዳደር አመራሮች፣  ቢሮ ሃላፊዎች፣ዞንና ወረዳ አስተዳደሪዎች ተሳተፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም