በትግራይ ክልል ሕዝቡ ማምረትና የራሱን ገቢ ማመንጨት እስከሚጀምር ሠብዓዊ ድጋፍ ይቀጥላል

64

አዲስ አበባ፣ ጥር 22/2013 ( ኢዜአ) በትግራይ ክልል እየተደረገ ያለው ሠብዓዊ ድጋፍ ሕዝቡ የራሱን ምርት ማምረት እስከሚጀምር ድረስ እንደሚቀጥል ብሔራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

በመቀሌ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት ኮሚሽነር ምትኩ ካሣ በሕግ ማስከበር ሂደት ጉዳት ላጋጠማቸው ወገኞች የሚሰጠው ሰብዓዊ ድጋፍ በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ተጠናክሮ መቀጠሉንና መንግስት ለዚህ በቂ አቅም እንዳለው ገልጸዋል፡፡ 

ሠብዓዊ ድጋፉ በትግራይ ክልል ሰባት ዞኖችና ከተማ አስተዳደሮችን ጨምሮ በሁሉም የገጠር ቀበሌዎች እየተዳረሰ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ 

እንደ ኮሚሽነር ምትኩ ገለጻ የጸጥታ ችግር ባለባቸው አንዳንድ አካባቢዎች በወታደራዊ እጀባ ጭምር ሰብዓዊ ድጋፍ እየደረሰ ነው።

በትግራይ ክልል ሰብዓዊ ድጋፉን ለማዳረስ 88 ጣቢያዎች መቋቋማቸውንና እስካሁንም በ82 ጣቢያዎች ሰብዓዊ ድጋፍ መከፋፈሉን ገልጸዋል፡፡

በተቀሩት ስድስት ጣቢያዎች ለመድረስም የምግብ ቁሳቁሶች ማጓጓዝ መጀመሩን ጠቁመዋል፡፡

ከሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦቱ ጎን ለጎን በክልሉ ይካሄዱ የነበሩ የልማት ስራዎችን ወደነበሩበት ሁኔታ ለመመለስ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

የመስኖ ስራ ለማስጀመር የክልሉ ግብርና ቢሮ ለአርሶ አደሮች የግብዓት አቅርቦት ለማድረስ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ 

ኮሚሽነር ምትኩ በትግራይ ክልል እየተደረገ ያለው ሰብዓዊ ድጋፍ ሕዝቡ ማምረት እስከሚጀምርና የራሱን ገቢ ማመንጨት እስኪችል ድረስ ይቀጥላል ነው ያሉት። 

በትግራይ ክልል ሰባት ወረዳዎች ለሚገኙ ነዋሪዎች የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት ስራው ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም