ሠብዓዊ ድጋፉ በበቂ ሁኔታ እየደረሰን ነው - የአይደር ክፍለ ከተማ ነዋሪዎች

104

አዲስ አበባ፣ ጥር 22/2013 ( ኢዜአ) መንግስት እያቀረበ የሚገኘው ሠብዓዊ ድጋፍ በበቂ ሁኔታ እየደረሳቸው መሆኑን በመቀሌ ከተማ የአይደር ክፍለ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

አስተያየታቸውን የሰጡ ነዋሪዎች በመንግስት የመጣላቸው ድጋፍ በአስቸጋሪ ወቅት በመድረሱ መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡ 

በሕግ ማስከበሩ ወቅት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ማለፋቸውንና አሁን እርዳታ በማግኘታቸው እፎይታ እንደተሰማቸው ተናግረዋል፡፡ 

ምግብ ነክ ቁሳቁስና የወጥ እህሎችን ጨምሮ ለኑሮ የሚያስፈልጉ ግብዓቶች ማግኘታቸውንም አክለዋል።

ቀደም ብሎም ተመሣሣይ ድጋፍ እንደደረሳቸው የገለጹት ነዋሪዎቹ ድጋፉ በከተማዋ በርካታ ቦታዎች መከፋፈሉን፤ በመጠንም ከፍ ያለና ለልጆቻቸውም በቂ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ነዋሪዎቹ በቀጣይ የሚፈልጉት ተደጋጋሚ እርዳታ ሳይሆን የአካባቢው ሠላም ይበልጥ ተረጋግቶ ወደ ቀደመ ስራቸው መመለስ እንደሆነም ለኢዜአ ተናግረዋል።

በማኅበረ ረድኤት ትግራይ የሰብዓዊ ድጋፍ ሰጪ አስተባባሪ የሆኑት አቶ ደስታለም ገብረጻድቃን በመቀሌ ከተማ በሚገኙ ከ40 በላይ ጣቢያዎች ከ80 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ሰብዓዊ ድጋፍ ተሰጥቷል ይላሉ፡፡ 

በአይደር ክፍለ ከተማ ሠርጸ ተብሎ በሚጠራው ጣቢያ ለ7 ሺህ 200 ሰዎች ለሁለት ወራት የሚያገለግል የምግብ ድጋፍ መደረጉን ገልፀዋል። 

በሠብዓዊ ድጋፉ ስንዴ፣ ዱቄትና ዘይት ጨምሮ ሌሎች ግብዓቶች ተካተዋል ብለዋል።

ለትግራይ ክልል እርዳታ እየደረሰ አይደለም በማለት የሚያወሩ አካላት ትክክል እንዳልሆኑና ሰብዓዊ ድጋፉ በትክክል እየደረሰ ስለመሆኑም አረጋግጠዋል።

በትግራይ ክልል ሠብዓዊ ድጋፍ የማዳረስ ስራው ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም